የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለ6ተኛ ሀገር ዐቀፍ ምርጫ ተግባራትን ማከናውን እንደ ጀመረ ይታወቃል፡። በዚህም መሠረት ከክልል መስተዳድሮች እና የከተማ መስተዳድሮች የሚጠበቁ የትብብር ግዴታዎች ለሁሉም የሚመለከታቸው አካላት መግለጹ ይታወሳል። ስለዚሁ ጉዳይ ጥር 10 ቀን 2013 ዓ.ም ቦርዱ ባወጣው መግለጫ የሚያስፈልገው ትብብር እንዳልተሟላ እና የምርጫ ክልል ቢሮዎችን ለመክፈት ዝግጅት ማድረግ እንዳልተቻለ አሳውቆ ነበር።

ቦርዱ ይህንን ካሳወቀበት ቀን አንስቶ ከፍተኛ መሻሻሎች የታዩ ሲሆን ከነዚህም መካከል

• አዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር

• ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት

• ድሬዳዋ ከተማ መስተዳድር

• ጋምቤላ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት

• ኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት

• ሐረሪ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ሙሉ ለሙሉ አስፈላጊ የሆኑትን ለምርጫ ክልል እና ለዞን ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ሊያገለግሉ የሚችሉ ቢሮዎችን አዘጋጅተው ለቦርዱ አሳውቀዋል። ለዚህም ቦርዱ ከፍተኛ ምስጋናውን ያቀርባል፡፡

በሌላ በኩል ቀሪዎቹ የክልል መስተዳድሮች በከፊል በተወሰኑ የምርጫ ክልሎች ቦታዎችን ያሳወቁ ሲሆን ሙሉ ለሙሉ አሟልተው ማቅረብ ግን አልቻሉም። በዚያ መሠረት ቦርዱ የዕጩዎች ምዝገባ የሚጀምርባቸውን ክልሎች ለመወሠን ተገድዷል። በመሆኑም በጊዜ ሠሌዳው በተቀመጠው ቀን መሠረት ከየካቲት 08 – 21 ቀን 2013 የዕጩ ምዝገባ የሚከናወነው ከላይ በተጠቀሱት ክልልሎች የሚገኙ ምርጫ ክልል ቢሮዎች ሲሆን በቀሪዎቹ ክልሎች የክልል መስተዳድሮቹ አስፈላጊውን ትብብር ሲያደርጉ ምዝገባው የሚጀመርበትን ቀን የሚያሳውቅ መሆኑን ያሳውቃል። በተጨማሪም ቀሪ ክልሎች ማለትም

• አፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት

• አማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት

• ሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት

• ደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት

• ሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት እስከ የካቲት 05 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ የተጠየቁትን አጠናቀው እንዲያቀርቡ በጥብቅ ያሳስባል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

የካቲት 01 ቀን 2013 ዓ.ም