Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከባለድርሻ አካላት ጋር በሁለት ረቂቅ መመሪያዎች ላይ ውይይት አደረገ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ውይይት ያደረገባቸው ሁለት ረቂቅ መመሪያዎቹ፤ በምርጫ ወቅት የኮቪድ 19 ሥርጭትን ለመቀነስና በምርጫ ሂደት ላይ ሰላምና ፀጥታን የሚያስከብሩ የፀጥታ አስከባሪ አካላት የአሠራር ሥርዓት እና የሥነ-ምግባር ድንጋጌዎችን የያዙ ናቸው። የመጀመሪያው የውይይት መድረክ ባሳለፍነው ሳምንት ጥር 14 ቀን 2013 ዓ.ም ከጤና ባለሞያዎች፣ ከፓለቲካ ፓርቲዎችና ከፀጥታ አካላት ጋር የተደረገ ሲሆን፤ ቀጣዩና በዛሬው ዕለት ጥር 18 ቀን 2013 ዓ.ም የተደረገው ውይይት ደግሞ ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችና ከባለድርሻ አካላት ጋር ተደርጎ ውሏል።

በሁለቱም ቀን የተደረጉትን ውይይቶች በንግግር የከፈቱት የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ የሆኑት ብርቱካን ሚደቅሳ ሲሆኑ፤ በንግግራቸውም መመሪያዎቹ በምርጫ ወቅት ከቦታ ቦታ መዘዋወር ስለሚኖር የኮቪድ 19 ሥርጭትን መቀነስ ለማስቻል፣ ከሁሉም ወገን ምን ይጠበቃል የሚለውንና ይህም ሲሆን የመራጩንና የፖለቲካ ፓርቲዎችን በነፃነት የመንቀሳቀስ መብት ላይ ጫና በማያሳድር እንዲሁም የአስፈጻሚ አካላትንና የታዛቢዎችን መብት ባከበረ መልኩ እንዲሆን ታስቦ የተዘጋጀ እንደሆነ አብራርተዋል። ከውይይቱ ተሳታፊዎች የሚገኙ ግብዓቶችን አስፈላጊነት የገለጹት ብርቱካን ከላይ የተጠቀሱትን ሁለት መመሪያዎች ለማዘጋጀት የተሣተፉትን የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሞያዎችንም አመስግነዋል።

የመጀመሪያውን ቀን ውይይት የመሩት የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ የሆኑት ውብሸት አየለ ሲሆኑ፤ የሁለተኛውንና በዛሬው ዕለት የተደረገውን ውይይት ደግሞ የቦርዱ አመራር የሆኑት ብዙወርቅ ከተተ መርተውታል። በሁለቱም ቀን ውይይቶች ላይ የቦርዱ የሕግ ክፍል ባልደረባ በሆኑት ወንጌል አባተ አማካኝነት መመሪያዎቹ ላይ ሰፊ ማብራሪያ ተሰጥቶበት መድረኩ ለተሳታፊዎች ክፍት የተደረገ ሲሆን፤ ከመድረኩም ሁለቱም መመሪያዎች ላይ ሀሳብ አስተያየት ተሰጥቶበታል። ለመጀመሪያው ቀን ውይይት ከመድረኩ ለተሰጡት አስተያየቶች በሕግ ባለሞያው ወንጌል አባተ፣ የምርጫ ቦርድ የኮቪድ 19 አስተባባሪ በሆኑት ዶ/ር ኢማን አብዱልሀኪምና በቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ አማካኝነት ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል። በተመሳሳይ መልኩ በዛሬው ዕለት ከመድረኩ ለተነሡት አስተያየቶች በአቶ ወንጌል አባተና በዶ/ር ኢማን አብዱልሀኪም አማካኝነት ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል።

በሁለቱም ቀን ውይይቶች በተደረገው ሁለተኛ ዙር ምክክር፤ በቦርዱ ማቋቋሚያ ዐዋጆ ቁጥር 1133/2011 አንቀጽ 7 ንዑስ አንቀጽ 11 እና አንቀጽ 8 ንዑስ አንቀጽ 1 እንዲሁም የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ሥነ-ምገባር ዐዋጅ ቁጥር 1162/2011 አንቀጽ 163 ንዑስ አንቀጽ 2 በተሰጠው ሥልጣን መሠረት በወጣው የምርጫ ፀጥታ አስከባሪ አካላት የአሠራር ሥርዓት እና የሥነ-ምግባር መመሪያ ላይ በሕግ-ባለሞያው ሰለሞን ግርማ አማካኝነት ሠፊ ገለጻ የተሰጠበት ሲሆን፤ ገለጻውን ተከትሎ ከመድረኩ ሀሳብ አስተያየት ተሰጥቶበታል። በመድረኩ መመለስ የሚችሉትን አስተያየቶች ሰለሞን ግርማ አማካኝነት መልስ ተሰጥቶባቸውና ግብዓት ተሰብስቦ የፕሮግራሞቹ መጠናቀቂያ ሆኗል፡፡

NEBE/Stakeholders

 

Share this post