በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ምዝገባ ሂደት በሚያከናውንበት ወቅት የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ስነምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 ዓ.ም. እና በመመሪያ ቁጥር 3 መሠረት በጠቅላላ ጉባኤ በማድረግ እስከ ጥር 30 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ እንዲያቀርቡ የተገለፀላቸው ፓርቲዎች እንደነበሩ ይታወሳል። ቦርዱ በ2012 ዓ.ም. ሊያካሂድ የነበረው 6ኛ አገራዊ ምርጫ በአለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተውን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ስጋት ምክንያት ተላልፎ የነበረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት የ6ኛውን አገራዊ ምርጫ የጊዜ ሰሌዳ ይፋ ሆኖ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ።
ነገር ግን ጥር 30/2013 ዓ.ም. ድረስ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲያካሂዱ የተገለፀላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች በተጠቀሰው ጊዜ ጠቅላላ ጉባኤ ማካሄዱ በሚያደርጉት የምርጫ ዝግጅት እንቅስቃሴ ላይ ጫና እንደሚፈጥርባቸው ገልፀው ምርጫው ከተጠናቀቀ በኋላ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲያካሂዱ እንዲፈቀድላቸው ለቦርዱ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ ቦርዱ ጥር 7 ቀን 2013 ዓ.ም. ባካሄደው ስብሰባ የፖለቲካ ፓርቲዎች እስከ ጥር 30/1013 ዓ.ም. ድረስ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲያካሂዱ ያሳለፈውን ውሣኔ እንዲራዘምላቸው ያቀረቡትን ጥያቄ መርምሯል፡፡
በዚሁ መሠረት ቦርዱ የ6ኛውን አገር አቀፍ ምርጫ አፈፃፀም የጊዜ ሰሌዳ አውጥቶ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ የገባ በመሆኑ በአሁኑ ወቅት የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባኤ ቢያካሂዱ ጫና የሚፈጠርባቸው መሆኑን ግምት ውስጥ በማስገባት 6ኛው ዙር ጠቅላላ ምርጫ በተጠናቀቀ በሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ ጠቅላላ ጉባኤ አካሂደው መተዳደሪያ ደንባቸው ላይ ማስተካከያ በማድረግ እንዲያቀርቡ ወስኗል፡፡ በመሆኑም ምርጫ ተሳትፎ ዝግጅት ምክንያት ጠቅላላ ጉባኤ ማድረግ ያልቻላችሁ የፖለቲካ ፓርቲዎች 6ተኛው አገር አቀፍ ምርጫ በተጠናቀቀ በሶስት ወር ውስጥ ጠቅላላ ጉባኤያችሁን በማከናወን ማሻሻያዎቻችሁን ለቦርዱ እንድታቀርቡ እያሳሰብን፣ ይህ ውሳኔ ተግባራዊ የሚሆነው በ6ተኛው አገራዊ ምርጫ ላይ የሚሳተፉ ፓርቲዎች ላይ ብቻ መሆኑን እናሳውቃለን።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ