Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የምርጫ ጉዳዮችን የሚመለከቱ ችሎቶች ምሥረታ ሂደት ያለበትን ደረጃና በዚህ ረገድ ከባለድርሻ አካላት የሚጠበቁ የተለያዩ ሚና እና ኃላፊነቶች ላይ ከፍርድ ቤቶች ፕሬዘዳንቶች ጋር ውይይት አደረገ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዛሬ ጥር 3 ቀን 2013 ዓ.ም የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ውብሸት አየለና የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት አቶ ሰለሞን አረዳ በተገኙበት ከክልል ፍርድ ቤቶች ፕሬዝዳንቶችና ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር የምርጫ ጉዳዮችን የሚመለከቱ ችሎቶች ምሥረታ ሂደት ያለበትን ደረጃና በዚህ ረገድ ከባለድርሻ አካላት የሚጠበቁ የተለያዩ ሚና እና ኃላፊነቶች ላይ ውይይት አደረገ። መድረኩ አቶ ውብሸት አየለና አቶ ሰለሞን አረዳ በተከታታይ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር የተከፈተ ሲሆን፤ አቶ ውብሸት በንግግራቸው የመድረኩን አስፈላጊነት ገልጸው የቦርዱንና የፍርድ ቤቶችን የጋራና የተናጠል ኃላፊነቶች ለያይቶ ማየቱ እንዲሁም የቦርዱን የሥልጣን ኃላፊነት ወሠኑን መረዳት አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል። አቶ ሰለሞን አረዳ በበኩላቸው ምርጫ የሕግ የበላይነት መኖሩን ማረጋገጫ መሆኑን ገልጸው፤ የምርጫን ቅቡልነት ማረጋገጥ የሚቻለው የምርጫውን ፍትሐዊነት ማረጋገጥ ሲቻል ነው ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።

የመድረኩን የመክፈቻ ንግግር ተከትሎ የባለሞያዎች ማብራሪያ የቀጠለ ሲሆን፤ የሕግ ባለሞያ የሆኑት ጌታቸው አሰፋ (ዶ/ር) በምርጫ፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር ዐዋጅ ቁጥር 1162/2011 ላይ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፤ ጌታቸውን (ዶ/ር) ተከትሎ በምርጫ ጉዳዮች የአቤቱታ ሰሚ አካላት አወቃቀርን፣ አደረጃጀትና የሥልጣን ተዋረድን አስመልክቶ በህግ ባለሞያው በሰለሞን ግርማ ማብራሪያ ተሰጥቶበታል። የሁለቱ ባለሞያዎች ማብራሪያ እንዳበቃ በአቶ ተስፋዬ ንዋይ አወያይነት ከመድረኩ በርካታ ሀሳብ አስተያየቶች የተሰጡ ሲሆን፤ የክልል ፍርድ ቤቶች ፕሬዝዳንቶች የመድረኩን መዘጋጀት አመስግነው በቀጣይም የተለያዩ ተመሳሳይ መድረኮች መኖር እንዳለባቸው ገልጸዋል። ፕሬዝዳንቶቹ በዋነኛነት አሉብን ያሏቸውን የሎጀስቲክና የሃብት እጥረቶች የገለፁ ሲሆን፤ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት አቶ ሰለሞን አረዳ ያሉባቸውን ችግሮች መናገራቸው እየተናበቡ ችግሮችን ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት እንደሚረዳ ገልጸው በትብብር ችግሮቹን ለመፍታት ጥረት እንደሚደረግ ገልጸዋል። በሁለት ዙር የተለያዩ ጥያቄዎች እና ሃሳቦችም ቀርበዋል።

አቶ ሰለሞን አረዳ የመዝጊያውን ንግግር ያደረጉ ሲሆን፤ በውድድር መኻል አለመግባባቶች እንደሚኖሩ ጠቅሰው በተፎካካሪ ፓርቲዎችም መሃል በሚደረገው ውድድር ሊፈጠሩ የሚችሉት አለመግባባቶችም ከዚህ ተለይተው እንደማይታዮና ዋናው ነገር አለመግባባቶች ሲፈጠሩ ቀልጣፋና ውጤታማ ውሣኔዎችን ለመስጠት የሚያስችሉ በቂ ዝግጅቶች ማድረግ መቻል ነው ሲሉ አብራርተዋል። አክለውም ግንቦት ላይ ለሚደረግ ምርጫ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ክርክሮች የግድ ግንቦት ላይ ብቻ ያጋጥማል ማለት እንዳልሆነና ከወዲሁ ዝገጅት ማድረግ ያለውን አስፈላጊነት፤ መሰል መድረኮች መኖራቸውም በሀገር ዐቀፍ ደረጃ ወጥ የሆነ ዝግጀት ለማድረግ ትልቅ አስተዋዕኦ እንዳለቸው ገልጸው ለመድረኩ መሳካት አስተዋጽኦ ያደረጉ ባለድርሻ አካላትን አመስግነው የመድረኩን የማጠቃለያ ሰጥተዋል።

NEBE/Board members

 

Share this post