የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ (ቅንጅት) መሥራች አባላት ስም ዝርዝርን እንዲያጣራ ለፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ጥያቄ አቀረበ
የካቲት 27 ቀን 2012 ዓ.ም.
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በቀድሞ አዋጅ ተመዝግበው የሚገኙ የፓለቲካ ፓርቲዎች በአዲሱ ህግ ላይ ተቀመጡትን መሥፈርቶች እንዲያሟሉ መጠየቁ ይታወሳል። በዚህም መሠረት ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ በአዲሱ አዋጅ በተደነገገው መሠረት 7,214 (ሰባት ሺህ ሁለት መቶ አስራ አራት) ተጨማሪ መሥራች የፓርቲ አባላትን አስፈርሞ እስከ መጋቢት 3 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ እንዲያቀርብ ተገልጾለት ነበር። ፓርቲው ጥር 26 ቀን 2012 ዓ.ም. ከ8 ክልሎች የተሰበሰበ የመሥራች አባላት ፊርማ የያዘ ሰነድ ለቦርዱ አቀርቧል። በመሆኑም የቀረበው ሰነድ ላይ የሚከተሉትን ቦርዱ አስተውሏል፡፡
- ቦርዱ ከእያንዳንዱ ገጽ ላይ በተወሰደ እና ወካይ ሊሆን የሚችል ናሙና ባደረገው ማጣራት፣ ጥሪ ካደረገባላቸው 50 ፈራሚዎች መካከል፣ አንዱ ብቻ ፈርሞ ሲገኝ 49ኙ ግን በተለያየ ምክንያት ፊርማቸውን አለማኖራቸውን አረጋግጧል (አብዛኛው የተሳሳተ ስልክ ነው፣ አልፈረምኩም የሚሉ ምላሾችና የማይሠራ መስመር ሆነው ተገኝተዋል)።
- የፓርቲው ማመልከቻ ላይ የፓርቲው ሊቀመንበር ቢፈርሙም፣ የተሰበሰበው ፊርማ ቃለ መሃላ ላይ የፈረመው ሌላ ግለሰብ መሆኑን፣ ኃላፊነቱም አለመገለጹን።
- የአያት ስም ያላስመዘገቡ፣ ስለአባልነታቸው በፊርማቸው ያላረጋገጡ፣ እድሜ፣ ጾታ፣ የምዝገባ ቀናቸው የማይታወቅ ፈራሚ ስሞችም በጉልህ ተገኝተዋል፡፡
በአዋጅ ቁጥር 1162/2011 እና አዋጁን ለማስፈጸም የወጣው አዋጅ መሠረት በአባልነት ያልተመዘገበን ሰው የተመዘገበ በማስመሰል የሌለን ሰው እንዳለ ማስመሰል ሐሰተኛ ስምና ፊርማ ማዘጋጀት በጥብቅ የተከለከለ ነው፡፡ በአዋጁ መሠረት ቦርዱ ሊወስድ ከሚችላቸው ምዝገባን ከመከልከልና ከማገድ በተጨማሪ አግባብ ባለው የወንጀል ህግ መሠረትም ሊጠየቅ እንደሚችል የህጉ ድንጋጌዎች ያዛሉ፡፡
ቦርዱ ከላይ ከተጠቀሱት ምክንያቶች በመነሳት ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ (ቅንጅት) ያቀረባቸው የመሥራች አባላት ፊርማ ስም ትክክለኛ ለመሆናቸው ማረጋገጥ አልቻለም፡፡ ስለዚህም የፌደራል ፓሊስ ኮሚሽን ጉዳዩን ተመልክቶ ህጋዊ ማጣራት እንዲያደርግ በዛሬው ዕለት የካቲት 27 ቀን 2012 ዓ.ም. አስተላልፏል፡፡