Skip to main content

የሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ የመጨረሻ ውጤት

ኅዳር 24 2012  

የሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ የመጨረሻ ውጤት 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሲዳማ ሕዝበ ውሳኔን በኅዳር 10 ቀን 2012 ዓ.ም. ያስፈጸመ ሲሆን ኅዳር 13 ቀን 2012 ዓ.ም. የመጀመሪያ ደረጃ ውጤት ማሳወቁ ይታወሳል፡፡ ቦርዱ ከመጀመሪያ ደረጃው ውጤት በማስከተል የእያንዳንዱን የምርጫ ጣቢያዎች ውጤት በዝርዝር በመገምገም፣ የድምር እንዲሁም ሌሎች የምርጫ ውጤት አለመጣጣም (discrepancies) ያለባቸውን ጣቢያዎች በማየት ውሳኔ አስተላልፎ የሚከተለውን የመጨረሻ ውጤት አሳውቋል፡፡ በመሆኑም በአጠቃላይ ድምፅ ከተሰጠባቸው 1,692 ምርጫ ጣቢያዎች እና ተጨማሪ 169 ድምፅ መስጫ ጣቢያዎች መካከል በ235 የምርጫ ጣቢያዎች ላይ ቦርዱ የተለያዩ የድምርና የውጤት አለመጣጣም ችግሮች (discrepancies) አግኝቷል፡፡

እነዚህ ምርጫ ጣቢያዎች ላይ የተገኙት ችግሮች አስፈጻሚዎች ቁጥር በሚደምሩበት ወቅት የተገኘ የቁጥር ድምር ችግር እና ድምፅ የሰጡ መራጮች ድምፅ ከተመዘገቡ መራጮች ድምፅ ከፍተኛ የመሆን ችግሮች ናቸው፡፡ እንዲህ ዓይነት ችግሮች በሚያጋጥሙበት ወቅት የችግሩን ምንጭ ለማወቅ የድጋሚ ቆጠራ መደረግ ቢኖበትም፣ ቦርዱ በአማራጭ ውጤቶቹ መካከል ያለው የውጤት ልዮነት ከፍተኛ ከመሆኑ አንጻር በውጤቱ ላይ ለውጥ ስለማያመጣ፣ በሂደቱ ተአማኒነት ላይ ጥያቄ ስለማያስነሳ እንዲሁም የድጋሚ ቆጠራ በማዘዝ ውጤት ማሳወቂያ ጊዜው መጓተት የለበትም በሚል የድጋሚ ቆጠራ ማካሄድን አስፈላጊ ሆኖ አላገኘውም፡፡ በዚህም መሠረት ዓለም አቀፍ የምርጫ ውጤት አስተዳደር ልምድን፣ የምርጫው ዓይነት ሕዝበ ውሳኔ መሆኑን እና በተወሰኑ ጣቢያዎች የተፈጠረው አለመጣጣም በአጠቃላይ የድምፅ ሰጪዎች ድምፅ ላይ የሚያመጣውን ተጽእኖ ውስንነት ከግምት ውስጥ በማስገባት ቦርዱ ችግር ከተገኘባቸው ጣቢያዎችን ሁኔታ አይቶ የሚከተሉትን ውሳኔዎች ሰጥቷል፡፡

1. ከተመዘገበው መራጭ በላይ ድምፅ ተሰጥቶ የተገኘባቸው 127 ምርጫ ጣቢያዎች ላይ ያለ ውጤት እንዲሰረዝ፣
2. በቆጠራ እና በድምር ስሌት ስህተት ከተገኘባቸው ጣቢያዎች መካከል የታየው ልዩነት 10 ድምፅ እና ከዚያ በታች የሆኑ ልዮነቶች ዋጋ እንዳላቸው ድምፅ እንዲቆጠሩ፣ ነገር ግን በ10 ድምፅ በላይ የድምር ልዮነት የተገኘባቸው ጣቢያዎች ውጤት እንዳይካተት ወስኗል፡፡ በዚህም መሠረት 37 ምርጫ ጣቢያዎች በከፍተኛ የድምርና የስሌት ስህተት የተነሳ ውጤታቸው ተሰርዟል፡፡

በአጠቃላይ በማጠናቀቂያ ውጤቱ 164 ምርጫ ጣቢያዎች ላይ ያሉ ውጤቶች ከላይ በተጠቀሱት ሁለት ምክንያቶች የተነሳ እንዲሰረዙ የተደረገ ሲሆን 71 የምርጫ ጣቢያዎች ግን የድምር ልዮነቱ ከ10 ድምፅ በታች በመሆኑ ስህተት ቢኖራቸውም ውጤታቸው ዋጋ ኖሮት እንዲቀጥል ተደርጓል፡፡ እንደዚህ ዓይነት የውጤት አለመጣጣም ከፍተኛ ውድድር ባለባቸው እንደ አገር አቀፍ ምርጫ ያሉ ውድድሮች ላይ ቢፈጠሩ የሚኖራቸውን ተጽእኖ ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል በመረዳት ቦርዱ እነዚህ ችግሮች የተፈጠሩበትን ምክንያት የሚያጣራ የቴክኒክ ቡድን አቋቁሟል፡፡ የቴክኒክ ቡድኑ የማጣራት ውጤትን መሠረት አድርጎም ለቀጣዩ ምርጫ አስፈላጊውን የአቅም ግንባታ ሥራዎችን፣ የአስፈጻሚዎች ስልጠና እና የምርጫ ሂደቱን የማሻሻል ሥራዎችን እንደሚሰራም ለመግለጽ ይወዳል፡፡

በመጨረሻም ሙሉ ለሙሉ የተጠናቀረው የሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ ውጤት የሚከተለው ሲሆን ዝርዝሩ ከዚህ መግለጫ ጋር በተያያዘው የውጤት መግለጫ ዝርዝር ፋይል ላይ ይገኛል፡፡

የተመዘገቡ መራጮች ቁጥር - 2,304,577
ድምፅ የሰጡ መራጮች ቁጥር - 2,279,022
በመቶኛ - 98.8911%
ድምፅ ያልሰጡ መራጮች ቁጥር - 25,555
በመቶኛ - 1.10888%
አጠቃላይ ውጤት
ዋጋ አልባ ድምፅ መስጫ ወረቀት - 16,624
ለሻፌታ (ለሲዳማ ክልልነት መደራጀት ድምፅ የሰጡ) መራጮች ቁጥር - 1,984,283
በመቶኛ - 97.7%
ለጎጆ (በደቡብ ክልል ለመቆየት ድምፅ የሰጡ) መራጮች ቁጥር - 30,018
በመቶኛ - 1.478%
የተሰረዘ ድምፅ - 248,097
የውጤቱ ዝርዝር በዚህ ማስፈንጠሪያ በመጫን ማየት ይችላሉ፡፡


የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

 

Share this post