Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የተቋቋሙ ልዩ ምርጫ ጣቢያዎች ላይ መራጮች ስለሚመርጡበት አግባብ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተወያየ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የተቋቋሙ ልዩ ምርጫ ጣቢያዎች ላይ መራጮች ስለሚመርጡበት አግባብ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ግንቦት 11 ቀን 2018 ዓ.ም. ተወያየ። የውይይቱን የመክፈቻ ንግግር የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ `ኃይሉ ያደረጉ ሲሆን፤ በንግግራቸውም ቦርዱ አካታችነትን በሁሉም አንጻር ለማረጋገጥ በርካታ ሥራዎችን ሲሠራ እንደነበር ተናግረው፤ እንደማሳያነት 7ኛው ጠቅላላ ምርጫን ከሚያስፈጽምባቸው ምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ ልዩ ምርጫ ጣቢያ ተቋቁሞላቸው የመራጮች ምዝገባ ያደረጉ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች እና ወታደራዊ ካምፖች እንዲሁም በድረ-ገጽ ላይ አማራጭ የመራጮች ምዝገባ ያከናወኑ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ጠቅሰዋል።

ሜላትወርቅ ቦርዱ በቀጣይ የሚያስፈጽመው ድምፅ የመስጠት ሂደት በተጠቀሱት አካባቢዎች በምን አግባብ መፈጸም አለበት የሚለው ላይ ከፍተኛ ጥናትና ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱን፤ በዚኽም በድረ-ገጽ ላይ የተመዘገቡ ተማሪዎች ወደየ አካባቢዎቻቸው ሄደው ድምፅ እንዲሰጡ፣ ተፈናቃዮችም በየካምፖቻቸው ሆነው ድምፅ የእንደሚሰጡ ለዚኽም አስፈላጊው ሎጀስቲክ ዝግጅት ሥራው እንደተጠናቀቀ፣ የወታደራዊ ካምፖች ላይ እንዴት ባለ አግባብ ተፈጻሚ መሆን ይችላል የሚለው ላይ ደግሞ ከተሣታፊዎች ጋር ለመወያየት መድረኩ እንደተዘጋጀ ተናግረዋል።

የሰብሳቢዋን ንግግር ተከትሎ የቦርዱ የኦፕሬሽን ሥራ ክፍል ኃላፊ በሆኑት በብሩክ የወንደሰን አማካኝነት አጠቃላይ በወታደራዊ ካምፕ ስለሚኖረው የድምፅ አሰጣጥ ሥነ-ሥርዓት ማብራሪያ የተሰጠ ሲሆን፤ ማብራሪያው ላይ ከተሣታፊ ፖለቲካ ፓርቲዎችና ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮች የተለያዩ አስተያየቶች ተወስደዋል።

በውይይቱ የማጠቃለያ ንግግራቸው ሜላትወርቅ፤ የተማሪዎች ምዝገባ በድረ-ገጽ አማራጭ የመሥራቱ ሂደት አጠቃላይ የመራጮች ምዝገባ መጠናቀቅን ተከትሎ የተጀመረ እንደመሆኑ መጠን ተማሪ ያልሆኑ ሰዎች እንዳይመዘገቡ ጥንቃቄ የተሞላበት የማረጋገጥ ሥራ እንደተሠራ፤ ድምፅ የመስጠት ሂደቱ ግን በአካል በየአካባቢያቸው በመሄድ እንደሚከናወን፣ ወታደርን ከካምፕ ወጥተኽ መርጠኽ ተመለስ ማለት ግን ከወታደራዊ ደኅንነት ተፈጥሯዊ ባህሪ አንጻር የማይቻል በመሆኑ ድምፅ የመስጠት ሂደቱ ባሉበት ካምፕ እንደሚሆን ተናግረዋል።

በመጨረሻም ፖለቲካ ፓርቲዎችና ሲቪል ማኅበራቱ ቦርዱ ለሚያስተዋውቃቸው አዲስ የአሠራር ሥርዓቶች የሚያሳዩት በጎ አስተያየት የሚመሰገን መሆኑን ተናግረው፤ በዕለቱም የተሰጡ ግብዓቶች ለድምፅ መስጫ ቀን የቀረው ጥቂት ቀናት ብቻ መሆኑ ከግምት ውስጥ ገብቶ ሕጉና ያለው ጊዜ ከግምት ውስጥ ገብቶ ተፈጻሚ እንዲሆን ቦርዱ እንደሚሠራ ተናግረዋል።

Share this post