ቦርዱ ሥምሪት የሰጣቸው የክትትል ቡድኖች 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የሚካሄድባቸውን አካባቢዎች የፀጥታ ሁኔታን በተመለከተ ዝርዝር ሪፖርት አቀረቡ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጥር 25 ቀን 2018 ዓ.ም. 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የሚካሄድባቸው አካባቢዎችን የፀጥታ ሁኔታ በተመለከተ አምስቱም የቦርድ አመራር አባላት፣ የክልል ርዕሰ መስተዳድሮችና የከተማ መስተዳድር ከንቲባዎች፣ የፌደራልና የክልል የፀጥታ ተቋማት አመራሮች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮች በተገኙበት ውይይት ማካሄዱን ተከትሎ የአካባቢዎቹን የፀጥታ ሁኔታ አስመልክቶ የተለያዩ ውይይቶችን በተለያየ ጊዜ ከባለድርሻ አካላት ጋር ሲያደርግ ቆይቷል።
ቦርዱ ጥር 25 ቀን 2018 ዓ.ም. ከክልል መንግሥታትና ከከተማ መስተዳድሮች እንዲሁም ከፀጥታ ተቋማት የተሰበሰበውን በአረንጓዴ፣ በቢጫና በቀይ የተፈረጀ የፀጥታ ሁኔታን የሚያሳይ መረጃ ላይ ተመሥርቶ ባለድርሻ አካላትን ከማወያየቱ በተጨማሪ፤ በአካባቢዎቹ ላይ ከሚወዳደሩ ፖለቲካ ፓርቲዎችም እንዲሁ ፀጥታውን የተመለከተ ሪፖርት በመውሰድ የመንግሥት አካላት ካቀረቡት የፀጥታ ሪፖርት ጋር ልዩነት ያላቸውን በመለየት መጋቢት 28 ቀን 2018 ዓ.ም. በአካባቢዎቹ ላይ ያለውን ተጨባጭ የፀጥታ ሁኔታና የፖለቲካ ምኅዳር ክትትል አድርጎ ሪፖርት የሚያቀርብ ቡድን ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እንዲሁም ከቦርዱ የተውጣጣ የክትትል ቡድን አዋቅሮ ሥምሪት መስጠቱ ይታወቃል። የሥምሪት ቡድኑም ክትትል ሲያደርግ ቆይቶ ሪፖርቱን ግንቦት 6 ቀን 2018 ዓ.ም. በይፋ ለቦርዱና ለባለድርሻ አካላት በልዩ መድረክ አቅርቧል።
የዚኽን መድረክ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ ሲሆኑ፤ በንግግራቸውም የፀጥታ ሁኔታውን አስመልክቶ መሬት ላይ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ እንዲከታተልና ሪፖርት እንዲያቀርብ ሥምሪት የተሰጠው ቡድን ሥራውን አጠናቆ መምጣቱን አመስግነው፤ መድረኩ አስፈላጊ የሆነበት ዋነኛ ምክንያት ቡድኑ የደረሰበትን ሪፖርት ሰምቶ ቀጣይ አቅጣጫ ለማስቀመጥና ከማን ምን ይጠበቃል የሚለውን ለመወያየትና ምክረ-ሐሳብ ለመውሰድ መሆኑን ተናግረዋል።
የሰብሳቢዋን ንግግር ተከትሎ የቀረበውን ሪፖርት በዘጠኝ ቡድን የተዋቀረው የክትትል ቡድን ያቀረበ ሲሆን፤ በሪፖርቱም ከፀጥታ ሁኔታ በተጨማሪ የየአካባቢዎቹ የፖለቲካ ምኅዳር፣ ፓርቲዎች በነፃነት ተንቀሳቅሰው የምርጫ ሥራቸውን ለመሥራት ምን ያኽል አስቻይ ሁኔታ አለ የሚለውን፣ ለምርጫው ያለው የሕዝብ ተነሣሽነትና የምርጫ ካርድ አወሳሰድ ሁኔታን ጨምሮ በርካታ የምርጫ ነክ ጉዳዮች ተዳሰውበታል።
በሪፖርቱቶቹ በአብዛኛዎቹ አካባቢዎች ላይ ምርጫ ለማድረግ አስቻይ ሁኔታ መኖሩን የተረጋገጠ ቢሆንም፤ አሁንም ትኩረት የሚሹ ቦታዎች መኖራቸው ተገልጿል። ሪፖርቱን አስመልክቶ የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ እና ምክትል ሰብሳቢ የሆኑት ተስፋዬ ንዋይ ተሣታፊውን ያወያዩ ሲሆን፤ በውይይቱም ስለአጠቃላይ ሁኔታው፣ ስለፀጥታና መዋቅራዊ ተግዳሮቶች እንዲሁም መወሰድ ስላለባቸው የዕርምት ዕርምጃዎችና ቦርዱ በቀጣይ ጥብቅ ክትትል ማድረግ አለበት በሚለው ላይ ሰፊ ሃሳብና አስተያየት ተሰጥቶበታል።