በምርጫ ወቅት በሴቶች ላይ ሊደርስ የሚችል ጥቃትን ለመከላከልና ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል የአሠራር ሥርዓት ሠነድ አፀደቀ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በምርጫ ወቅት በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ለመከላከል የሚያስችል የአሠራር ሥርዓት (Standard Operating Procedure (SOP)) አፀደቀ። በአሠራር ሥርዓቱ ጥቃቱን በተመለከተ የትኞቹ ተቋማት ይመለከታቸዋል የሚለውን የባለድርሻ አካላት ልየታን ጭምር ያካተተ ሲሆን፤ ከነዚኽም ውስጥ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ የፍትሕ ሚኒስቴር፣ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን፣ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙ`ኃን ባለሥልጣን፣ ለምርጫ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኅብረት፣ የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር፣ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት እና የኢትዮጵያ ሴት የፖለቲካ ፓርቲ አባላት ጥምረት ይጠቀሳሉ።
ቦርዱን ጨምሮ ከላይ የተጠቀሱት 10 ተቋማት ኃላፊነታቸውን በቁርጠኝነት እንደሚወጡ ማረጋገጫ እና ማስተማመኛ ፊርማቸውን ያኖሩበትን መድረክ በንግግር የከፈቱት የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ ሲሆኑ፤ በንግግራቸውም ከሁሉም ተቋማት የመጡትን ተሣታፊዎች አመስግነው መድረኩ በምርጫ ወቅት በሴቶች ላይ የሚደርስን ጥቃት ቢቻል ለማስቀረት ካልሆነም ለመቀነስ እንዲቻልና ተከስቶም ሲገኝ ለምላሽ አሰጣጥ የተዘጋጀውን መደበኛ የአሠራር ሥርዓት ለማረጋገጥና ለማፅደቅ መሆኑን ተናግረዋል። የአሠራር ሥርዓቱ ምርጫ ጋር ተያይዞ የተዘጋጀ በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነና ልዩ ትርጉም የሚሰጠው መሆኑን ተናግረዋል።
“ሠነዱ በምርጫ ወቅት የሴቶችን ደኅንነት፣ ክብር፣ ዕኩልነትና ተሣትፎ ለማረጋገጥ የተዘጋጀ ቁርጠኝነትን ማሳያ ነው“ ያሉት ሰብሳቢዋ፤ ቦርዱ እንደ አዲስ ሲቋቋም በተቋሙ ውስጥ እንዲፈጠሩ ካደረጋቸው ሥራ ክፍሎች ውስጥ “የሥርዓተ-ፆታና ማኅበራዊ አካታችነት” አንዱ መሆኑን፤ በዚኽም ሳይወሠን በሁሉም ሥራ ክፍሎች ተፈጻሚ እንዲሆን የተለያዩ ፖሊሲዎችን በማውጣትና ሥልጠናዎችን በመስጠት ጭምር ሲሠራ መቆየቱን ተናግረዋል።
የሴቶችን በፖለቲካ የሚኖራቸውን ተሣትፎ ለማሻሻል ከተፈለገ ሁሉንም ዓይነት ፆታዊ ጥቃቶችን ተከታትሎ ምላሽ መስጠት ካልተቻለ ትርጉም እንደማይኖረውና ይኽም SOP በሴቶች ላይ በምርጫ ወቅት የሚፈጸምን ፆታዊ ጥቃት በተገቢው መልኩ ለመከላከል፣ ለመመዝገብና ተገቢ ምላሽ ለመስጠት እንዲሁም ጥቃት የደረሰበትን አካል ደኅንነት የማረጋገጥ ግልጽ የአሠራር ሥርዓት እንዳካተተ ተናግረዋል። ፊርማቸውን ካኖሩት 10 ተቋማት በቅንነት፣ በቅንጅትና በተጠያቂነት ስሜት መሥራት ይጠበቃል ብለዋል። ያ ሲሆን ሴቶች ያለሥጋትና በነፃነት የመሣተፍ ፍላጎታቸውን ማረጋገጥ እንደሚቻል ያላቸውን ዕምነት ገልጸዋል።
የሜላትወርቅን ንግግር ተከትሎ ሰፊ ውይይት በተሣታፊዎች መካከል የተደረገ ሲሆን፤ በመጨረሻም የፊርማ ማኖር ሥነ-ሥርዓት ተከናውኗል።