Skip to main content

ቦርዱ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለመወዳደር ለተመዘገቡ የግል ዕጩ ተወዳዳሪዎችን ነፃ የዓየር ሰዓት ድልድል ይፋ አደረገ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በትላንትናው ዕለት ሚያዚያ 8 ቀን 2018 ዓ.ም. በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በግል ዕጩነት ለመወዳደር የተመዘገቡ የግል ዕጩ ተወዳዳሪዎችን አወያይ። አምስቱም የቦርድ አመራር አባላት የተገኙበትን መድረክ በንግግር የከፈቱት የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉን ሲሆን፤ በንግግራቸውም፤ ቦርዱ 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ በጊዜ ሠሌዳው መሠረት ለማካሄድ ልዩ ልዩ የቅድመ-ምርጫ ተግባራትን እያከናወነ መሆንኑ አስታውሰው፤ የግል ዕጩ ተወዳዳሪዎች ነፃ የዓየር ሰዓት ድልድልም የዚኹ አካል መሆኑን ተናግረዋል። የውይይቱ አንዱ አጀንዳ የሆነው የነፃ የዓየር ሰዓት ድልድልን አስመልክቶ ሲናገሩም የግል ዕጩዎቹ በሚያደርጉት የምረጡኝ ቅስቀሳ ወቅት ሕጉን ተከትለው በኃላፊነት ስሜት መሆን እንዳለበትና ይኽም የምርጫውን ሰላማዊ፣ ፍትሐዊና ተዓማኒነት በማረጋገጥ ረገድ ትልቅ ድርሻ እንዳለው ተናግረዋል።

የሰብሳቢዋን ንግግር ተከትሎ የቦርዱ የሕግ ሥራ ክፍል ም/ኃላፊ የሆኑት ረድዔት ብሩ አጠቃላይ የምርጫ የሕግ ማዕቀፎችን አስመልክቶ ገለጻ የሰጡ ሲሆን፤ ቦርዱ በቅድመ-ምርጫ ወቅት የሠራቸውን ተግባራት አስመልክቶ ደግሞ የቦርዱ የኦፕሬሽን ክፍል ኃላፊ የሆኑት ብሩክ የወንደሰን አብራርተዋል። የምርጫ ቅስቀሳ ሥነ-ምግባር፣ ነፃ የዓየር ሰዓት አጠቃቀምና ድልድልን እንዲሁም ለጽጩዎች ስለሚከፋፈለው የገንዘብ ድጋፍ ስለተመለከቱት መመሪያዎች ደግሞ የሕግ ባለሞያ የሆኑት አይተነው ደበበ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ተሣታፊዎቹ በቀረቡት ገለጻዎች ላይ እንዲሁም ባጠቃላይ ከምርጫው ጋር ተያያዥነት ያላቸው ጥያቄዎችን የነሡ ሲሆን፤ ለቀረቡት ጥያቄወችና ማብራሪያ ለሚፈልጉ አስተያየቶች የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ ተስፋዬ ንዋይን ጨምሮ በቦርድ ሥራ አመራር አባላት ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል።

ነፃ የዓየር ሰዓት ድልድሉ ለየአንዳንዱ ወንድ የግል ዕጩ 15 ደቂቃ ርዝማኔ ያለው አንድ የቴሌቪዥን፣ አንድ የሬዲዮ እና አንድ የጋዜጣ ዐምድ በመረጧቸው መገናኛ ብዙኃን ላይ እንዲያስተላልፉ የሚያደርግ ሲሆን፤ የግል ዕጩዋ ሴት ስትሆን በሦስት የመገናኛ ብዙኃን የሥርጭት አማራጮች የሚሰጠው ነፃ የዓየር ሰዓት ድልድል በመረጠችው የሥርጭት አማራጭ አንድ ተጨማሪ ዕድል ይሰጣል። ሴት ሆና አካል ጉዳተኛ ስትሆን ደግሞ ተጨማሪ ዕድሉ ወደ አምስት ጊዜ ከፍ ይላል። ይኽው ድልድል ዕጩው ወንድ አካል ጉዳተኛ ሲሆን፤ በሦስት የሥርጭት አማራጮች ለአንድ ጊዜ የነበረው ነፃ የዓየር ሰዓት ድልድል በመረጠው የሥርጭት አማራጭ ላይ አንድ ተጨማሪ ዕድል ይሰጣል።

Share this post