ቦርዱ የ7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ የሚካሄድባቸው አካባቢዎች የፀጥታ ሁኔታን የሚከታተል ቡድንን ሥምሪትና ተግባራትን በተመለከተ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተወያየ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በትላንትናው ዕለት መጋቢት 28 ቀን 2018 ዓ.ም. የ7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ የሚካሄድባቸው አካባቢዎች የፀጥታ ሁኔታን የሚከታተል ቡድንን ሥምሪትና ተግባራትን በተመለከተ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተወያየ። የውይይቱን የመክፈቻ ንግግር የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ ያደረጉ ሲሆን፤ በንግግራቸውም ቦርዱ ቀደም ሲል ከመንግሥት የፀጥታ ተቋማ በመቀጠልም ከፖለቲካ ፓርቲዎች የተሰበሰበውን የፀጥታ ሁኔታ መረጃ መሠረት አድርጎ የተለያዩ ውይይቶችን ማካሄዱን አስታውሰው፤ የዚኽም ውይይት ዋና ዐላማ ቀደም ሲል የቀረቡ መረጃዎች መሬት ላይ ወርዶ በትክክል ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ በመመልከት ሁኔታውን የሚመለከት የክትትል ቡድንን ሥምሪትና ተግባራት ላይ መወያየት በማስፈለጉ እንደሆነ ተናግረዋል።
የመክፈቻ ንግግሩን ተከትሎ የቦርዱ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ማስተባበሪያ ኃላፊ የሆኑት ቀነኒ እንሰርሙ የአካባቢዎቹ የፀጥታ ሁኔታን አስመልክቶ የተለዩ አካባቢዎች ላይ የሚሠማሩ ከፖለቲካ ፓርቲ፣ ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እንዲሁም የቦርዱ ባለሙያዎች ያካተተ የክትትል ቡድን ስለሚሠማራበት አግባብና ዝርዝር ኃላፊነቶች አስመልክቶ ገለጻ የሰጡ ሲሆን፤ በማስከተልም ከፖለቲካ ፓርቲዎችና ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የተውጣጡ ተሣታፊዎች ሃሳብ አስተያየት ሰጥተውበታል። ከተሣታፊዎች ለተነሱት ጥያቄዎች የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ እንዲሁም ምክትል ሰብሳቢ ተስፋዬ ነዋይ ምላሽ ሰጥተዋል።
ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እንዲሁም ከቦርዱ የተውጣጣ የክትትል ቡድን በውይይቱ ዕለት የተዋቀረ ሲሆን፤ የክትትል ቡድኑ ኃላፊነት የፀጥታ ጉዳይን በተመለከቱ ጉዳዮች ሳይወሠን ፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት የሚያጋጥሟቸውን ተግዳሮቶችና አጠቃላይ የምርጫውን አፈጻጸም እንዲሁም ነፃ፣ ገለልተኛና ተዓማኒነቱን በተመለከተም ምልከታ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል::
ቦርዱ ቀደም ሲል ከክልል መንግሥታትና ከከተማ መስተዳድሮች እንዲሁም ከፀጥታ ተቋማት ያሰባሰበውን የምርጫ ክልሎችን ወቅታዊ የሰላምና ፀጥታ ጉዳይ የተመለከተ መረጃ መሠረት አድርጎ የፖለቲካ ፓርቲዎችን፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን፣ የክልል ርዕሰ መስተዳድሮችና የከተማ መስተዳድር ከንቲባዎች እንዲሁም የፌደራልና የክልል የፀጥታ ተቋማት አመራሮችን ያወያየ ሲሆን፤ ይኽንንም ተከትሎ በፖለቲካ ፓርቲዎች የፀጥታ ሥጋት አለባቸው ተብለው የተለዩ አካባቢዎችን አስመልክቶ የራሳቸውን ግምገማ አቅርበው ተጨማሪ ውይይቶች ቀደም ሲል ተደርገዋል።