Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የፖለቲካ ፓርቲዎች የክርክር መድረክ ማካሄድ ጀመረ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለሚወዳደሩ ፖለቲካ ፓርቲዎች ያዘጋጀው የክርክር መድረክ የቦርዱን ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉን ጨምሮ አምስቱም የቦርድ ሥራ አመራር አባላት በተገኙበት በይፋ ተጀመረ። መድረኩን በንግግር የከፈቱት ሜላትወርቅ ሲሆኑ፤ በንግግራቸውም ቦርዱ ይኽን የክርክር መድረክ ሲያዘጋጅ ፖለቲካ ፓርቲዎች ነፃ፣ ገለልተኛና ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ፖሊሲዎቻቸውንና ፕሮግራሞቻቸውን የሚያስተዋውቁበት መድረክን መፍጠር ብቻ ሣይሆን፤ መራጩም በዛው ልክ አማራጭ የፖሊሲ ሃሳቦችን የመስማት ዕድል ኖሮት እንዲወሥን ለማስቻል በማሰብ መሆኑን ተናግረዋል። በተጨማሪም ይኽ የክርክር መድረክ በመካሄድ ላይ ያለው የመራጮች ምዝገባ ላይ የበለጠ መነቃቃትን እንደሚፈጥር ተናግረው፤ መራጮችም በማንዋልና በዲጂታል አማራጭ በመካሄድ ላይ ያለው የመራጮች ምዝገባ ከመጠናቀቁ በፊት ተመዝግበው ካርድ እንዲወስዱ አስታውሰዋል።

ክርክሩ በመገናኛ ብዙኃን ባለሞያዎች፣ በፖለቲካ ምሁራን እንዲሁም በጥናት ባለሞያዎች ጭምር ተሣትፎ ለወራት ከፍተኛ ዝግጅት ሲደረግበት የነበረ ሲሆን፤ ጥያቄዎቹም የፖለቲካ ፓርቲዎችን ፕሮግራምና ማኒፌስቶ መሠረት አድርገው የተዘጋጁ ናቸው። ለክርክሩ የተመረጡ ርዕስ-ጉዳዮች አስቀድሞ ለፖለቲካ ፓርቲዎቹ ተልኮ ፍላጎታቸውን እንዲያሳውቁ የተደረገ ሲሆን፤ በአከራካሪነትና በጠያቂነት የሚሣተፉ ባለሞያዎችም ዝርዝር እንዲሁ ዝርዝራቸው ተልኮ የማሳወቅ ሥራ ተሠርቷል። በክርክሩም ወቅት የተነገሩ ሃሳቦችን እውነትነት የማረጋገጥ ሥራ የሚሠሩ ባለሞያዎች እንዲሣተፉ ተደርጓል።

Share this post