Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የሚደረግባቸው አካባቢዎችን የፀጥታ ሁኔታ በተመለከተ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ተወያየ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በትላንትናው ዕለት መጋቢት 2 ቀን 2018 ዓ.ም. 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የሚደረግባቸው አካባቢዎችን የፀጥታ ሁኔታ በተመለከተ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ተወያየ። የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉን ጨምሮ አምስቱም የቦርድ ሥራ አመራር አባላት በተገኙበት በተደረገው ውይይት ላይ ቦርዱ ቀደም ሲል ከፖለቲካ ፓርቲዎች የሰበሰበው ሥጋት አለባቸው ብለው የለዩዋቸው አካባቢዎች ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፤ በውይይቱ ከተነሡ ተጨማሪ አጀንዳዎች ውስጥም በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ ያለ የፀጥታ ሥጋትና በነፃነት የምረጡኝ ቅስቀሳ ያማድረግ ሁኔታ፣ የምርጫ አስፈጻሚዎች ያለምንም ተፅዕኖ ሥራቸውን ማከናወን፣ የፖለቲካ ምኅዳርን በተመለከተ የተቸገሩ መሆኑ ይጠቀሳሉ።

ሜላትወርቅ ቦርዱ በራሱ የደረሰባቸውንና የእርምት ዕርምጃ ሊወሰድባቸው ይገባል ያላቸው ጉዳዩችን የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ማስተካከያ እንዲያደርጉ የራሱን ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑን ገልጸው፤ አሁንም ፖለቲካ ፓርቲዎቹ በየለዩዋቸውና ለቦርዱ ባሳወቋቸው አካባቢዎች ላይ በቀጣይ የክትትልና ቁጥጥር ኮሚቴ እንደሚያሠማራ ተናግረዋል። ይኽም ከቦርዱ የምርጫ ክትትልና ቁጥጥር ቡድን፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የተውጣጡ ተሣታፊዎች እንደሚኖሩት አስታውሰዋል።

ቦርዱ ቀደም ሲል የክልል ርዕሰ መስተዳድሮችና የከተማ መስተዳድር ከንቲባዎች፣ የፌደራልና የክልል የፀጥታ ተቋማት አመራሮች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮች በተገኙበት፤ ቦርዱ ከክልል መንግሥታትና ከከተማ መስተዳድሮች እንዲሁም ከፀጥታ ተቋማት የሰበሰበውን በአረንጓዴ፣ በቢጫና በቀይ የተፈረጀ የፀጥታ ሁኔታ መረጃ ቀርቦ ውይይት እንደተደረገበት ይታወቃል።

Share this post