Skip to main content

ቦርዱ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የሚወዳደሩ ፖለቲካ ፓርቲዎችን የምርጫ መወዳደሪያ ምልክት ይፋ ባደረገበት መድረክ ላይ ፓርቲዎች የምርጫ ሥነ-ምግባር ደንብ ፈረሙ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባሳለፍነው ሣምንት መጠናቀቂያ ባዘጋጀው መድረክ ላይ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የሚወዳደሩ ፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ሥነ-ምግባር ደንብ ፈረሙ። ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት ተወካዮች እንዲሁም መገናኛ ብዙ`ኃን በተገኙበት፤ 48 ፖለቲካ ፓርቲዎች ለምርጫ የሚወዳደሩባቸውን ምልክቶች ይፋ ለማድረግ የተዘጋጀውን መድረክ በንግግር የከፈቱት የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ ሲሆኑ፤ በንግግራቸውም ቦርዱ የፖለቲካ ፓርቲዎችን የምርጫ መወዳደሪያ ምልክት ይፋ እስከሚያደርግበት ጊዜ ድረስ በነበረው የቅድመ-ምርጫ ተግባራቱ ምን ሲያከናውን እንደነበር ማብራሪያ ሰጥተዋል። የሥነ-ምግባር ደንቡን አስፈላጊነት አስመልክቶ ባደረጉት ንግግርም ምርጫ ነፃ፣ ሰላማዊና ፍትሐዊ ሆኖ የሚከናወነው ሁሉም ፓርቲ ሕግን አክብሮ ኃላፊነቱን ሲወጣ እንደሆነ፤ የምርጫው ስኬትም የሚረጋገጠውም ቦርዱ ለብቻው በሚያደርገው ጥረት ሣይሆን ሁሉም ባለድርሻ አካላት ዕኩል ኃላፊነቱን መወጣት ሲችል እንደሆነ በአጽንዖት ተናግረዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች የሥነ-ምግባር ደንብ መፈረምን ተከትሎ የሚኖረው የምርጫ ቅስቀሳ ሂደትና ቦርዱ በልዩ ሁኔታ እየተዘጋጀበት ያለው የተወዳዳሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች የክርክር መድረክ መሆኑ ይታወቃል። ይኽንንም አስመልክቶ ሜላትወርቅ ሲናገሩ “መገናኛ ብዙ`ኃኑ ሁሉም ፓርቲዎች ፖሊሲዎቻቸውንና ፕሮግራማቸውን ለሕዝብ እንዲያስተዋውቁ ያለአድልኦ ዕኩል ዕድል መስጠት ይጠበቅባቹሃል” ሲሉ አሳስበዋል።

የመክፈቻ ንግግሩን ተከትሎም የሁሉም ፖለቲካ ፓርቲዎች የመወዳደሪያ ምልክቶች ከነስያሜዎቻቸው ቀርበዋል። በመቀጠልም የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ ተሰፋዬ ንዋይ በሰባት ምዕራፎችና በ30 አንቀጾች የቀረበውን እንዲሁም ከፖለቲካ ፓርቲዎቹ ጋር አስቀድሞ ውይይት ተደርጎበት ሃሳብ የሰጡበትን የሥነ-ምግባር ደንብ አስፈላጊነት፤ እንዲሁም ዝርዝር አንቀጾቹ ምን እንዳካተቱ ጭምር ለመድረኩ ተሣታፊዎች ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተው ፖለቲካ ፓርቲዎቹ እንዲፈርሙበት ተደርጓል።

Share this post