Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በመራጮች ትምህርት ላይ ለሚሣተፉ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና መስጠት ጀመረ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በመራጮች ትምህርት ላይ ለሚሣተፉ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና መስጠት ጀመረ። ከዛሬ የካቲት 11 እስከ 12 ቀን 2018 ዓ.ም. የሚቆየውን ሥልጠና የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የቦርዱ የሥራ አመራር አባል የሆኑት ተኽሊት ይመስል ሲሆኑ፤ በንግግራቸውም የሲቪልና የመራጮች ትምህርት የአንድ ጊዜ ሥራ አለመሆኑን ተናግረው፤ የመራጮች ምዝገባ ሊጀምር ጥቂት ቀን እንደመቅረቱ መጠን ትኩረታችንን በመራጮች ትምህርት ላይ በማድረግ፤ መራጩ ሕዝብ የመራጭነት ካርዱን ከየካቲት 28 እስከ መጋቢት 28 ቀን 2018 ዓ.ም. በሚከናወነው የመራጮች ምዝገባ ወቅቱን ጠብቀው ካርድ እንዲወስዱና በምርጫ ቀንም እንዲሁ በዕውቀት ላይ ተመሥርተው ድምፅ እንዲሰጡ የሚያስችላቸውን ትምህርት መስጠት እንደሚገባ ተናግረል። ቦርድ የመራጮች ትምህርት ለመስጠት የሚያስችለውን ማንዋል አሻሽሎ እንዳቀረበና ማኅበራቱም ትምህርቱን በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት እንደሚሰጡ ያላቸውን ዕምነት ገልጸዋል።

የሲቪክ እና የመራጮች ትምህርት መሠረታዊ ባህሪያትና መርኆቹ፣ የሲቪል ማኅበራት በምርጫ ዑደት ውስጥ የሚኖራቸው ሚናና አሠራራቸው፣ ብዝኅነትን መረዳት፣ ልዩነትን ማክበርና አካታችነት፣ ውጤታማ ማኅበረሰብን የማስተባበር ሥነ-ዘዴ፣ በመራጮች ትምህርት የበጎ ፈቃደኞች እንቅስቃሴ እና ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጋር በጋራ የሚሠሩበት አግባብ፣ የምርጫ የሕግ ማዕቀፎችና የምርጫ ቦርድ ኃላፊነት፣ የተለያዩ ሕዝባዊ ስብሰባዎችና መሰል ሁነቶች ላይ ንግግር የማድረግ ሥልጠናው ትኩረት ካደረገባቸው ርዕሰ-ጉዳዮች ውስጥ ተጠቃሽ ናቸው።

በሥልጠናው ወቅት በስምንት ምዕራፍ የተከፋፈለውን ቦርዱ ያሻሻለው “የሥነ-ዜጋና የመራጮች ትምህርት ማስተማሪያ ማንዋል” ለተሣታፊዎች የተሰጠ ሲሆን፤ ቦርዱ ቀደም ሲል በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በመራጮች ትምህርት ላይ ለሚሠማሩ 169 የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ዕውቅና መስጠቱ ይታወቃል።

Share this post