የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በበጎ ፈቃደኝነት ለሚሠማሩ ወጣቶች ሥልጠና ሰጠ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የተለያዩ የቅድመ ምርጫ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል። ከነዚኽም ተግባራት አንዱ ዜጎች በዕውቀት ላይ የተመሠረት ምርጫን እንዲያደርጉ የሚያስችላቸውን የሥነ ዜጋ እና የመራጮች ትምህርት መስጠት በዋንኛነት ይጠቀሳል። በመሆኑም የቦርዱ የሥነ ዜጋ እና የመራጮች ትምህርት ሥራ ክፍል ከቦርዱ የክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ጋር በመተባበር አዲስ አበባ እና በድሬደዋ ከተማ መስተዳደሮችን ጨምሮ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ በጋምቤላ፣ በሐረሪ፣ በአፋር፣ በሶማሊ፣ በደቡብ ኢትዮጵያ፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ እና በሲዳማ ክልሎች በመራጮች ትምህርት እና በመረጃ ሥርጭት ዘመቻ ሥራዎች ላይ ለሚሣተፉ 775 በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች የሁለት ቀናት ሥልጠና ሰጥቷል።
የበጎ ፈቃደኝነት ፅንሰ-ሐሳብ፣ የሥነ-ዜጋና የመራጮች ትምህርት ምንነት እንዲሁም አንድነት እና ልዩነት እና ትምህርቱ የሚሰጥበት ሥነ-ዘዴ፣ መርኆች እና የማኅበረሰብ ክፍሎች ልየታ፣ የዴሞክራሲ ሥርዓት እና የዜጎች ተሣትፎ፣ የምርጫ ሥርዓት እና ዑደት ፣ የባለድርሻ ኣካላት እና የመራጮች ተሣትፎ ሥልጠናው ትኩረት ካደረገባቸው ዋና ዋና ርዕሰ-ጉዳዮች ውስጥ ይጠቀሳሉ። የሥራ ክፍሉ ለበጎ ፈቃደኞች ሥልጠና ሲሰጥ ይኽ ለሁለተኛ ጊዜ ሲሆን፤ ከዚህ ቀደም በተለያዩ ቦታዎች ለሚገኙ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሥልጠናው መሰጠቱ ይታወቃል።
ቦርዱ እነዚህን በሁለት ዙር ያሠለጠናቸውን በጎ ፈቃደኞች ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በመራጮች ምዝገባ ወቅት የመራጮች ትምህርት እና በምርጫ ቀን የመራጮች መረጃ ሥርጭት ዘመቻ ሥራዎችን እንዲያከናውኑ በተለያዩ ቦታዎች ለማሠማራት ያቀደ ሲሆን፤ ሠልጣኞቹ በተለይም ዜጎች በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ምርጫን እንዲያደርጉ ከማስተማር እንዲሁም ቦርዱ ያለማውን የዲጂታል የመራጮች መመዝገቢያ አማራጭን በሰፊው ከማስተዋወቅ አንጻር ጉልኽ ሚና እንደሚኖራቸው ይታመናል።