ቦርዱ የፖለቲካ ፓርቲ ሲሰተም አሰተዳዳሪዎች በቦርዱ ባለሙያዎች ድጋፍ እየተደረገላቸው ዕጩዎቻቸውን እንዲመዘግቡ ማድረግ ጀመረ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የዕጩዎች ምዝገባን በምርጫ የጊዜ ሠሌዳው መሠረት ከጥር 1 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ በማከናወን ላይ መሆኑ ይታወቃል። ቦርዱ ቀደም ሲል ባሳወቀው መሠረት የፖለቲካ ፓርቲዎች ዕጩዎቻቸውን ሙሉ በሙሉ በዲጂታል ሥርዓት ታግዘው በመመዝገብ ላይ ያሉ ሲሆን፤ ይኽንንም ለማከናወን እንዲችሉ የሲስተም አስተዳዳሪ ወኪሎቻቸውን ለቦርዱ አሳውቀው በሁለት ዙር ለአራት ቀናት ሥልጠና እንዲወስዱ አድርጓል። ሥልጠናውን ከመስጠት በተጨማሪ በስልክ እንዲሁም የሲስተም አስተዳዳሪዎችን ያካተተ “ቴሌግራም ግሩፕ” በመክፈትም በምዝገባ ወቅት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ማንኛውንም ጥያቄዎቻቸውን ሲያስተናግድ ቆይቷል። ቦርዱ በተለያዩ አማራጮች የሲስተም አስተዳዳሪዎቹ የሚያከናውኑትን የዕጩዎች ምዝገባ ሲያስተባብር የነበረ ሲሆን፤ ከዛሬ ጥር 23 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ ደግሞ ለተከታታይ ሁለት ቀናት የሚቆይ በዋናው መሥሪያ ቤት በአካል ተገኝተው በቦርዱ የአይ.ሲ.ቲ ባለሞያዎች ቀጥተኛ ዕገዛ እየተደረገላቸው ዕጩዎቻቸውን እንዲመዘግቡ በማድረግ ላይ ይገኛል።
እስከ የካቲት 1 ቀን 2018 ዓ.ም. በሚቆየው የዕጩዎች ምዝገባ እስካሁን 41 በተናጠል እና 15 በሦስት የተለያዩ ጥምረቶች የቀረቡ ፖለቲካ ፓርቲዎች፤ ለምዝገባ አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎችን አሟልተው በሲስተሙ ላይ ዕጩዎቻቸውን መመዝገብ የሚያስችላቸው “አካውንት” ተፈጥሮላቸው ዕጩዎቻቸውን በመመዝገብ ላይ ይገኛሉ። ቦርዱ በቴክኖሎጂ የታገዘው የዕጩዎች ምዝገባ ሥርዓትን ለማስተዋወቅ ምክንያት ከሆኑት ውስጥ ባለፉት ምርጫዎች ወቅት ፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ክልል ጽ/ቤት በመቅረብ ዕጩዎችን ሲያስመዘግቡ ደረሰብን ያሉትን መንገላታት ጨምሮ ከማንኛውም ውጫዊ ተፅዕኖ ነፃ በማድረግ፣ ሠነዶች አሟልቶ ከማቅረብ አንጻር ያለውን ምልልስ በማስቀረት፣ በዕጩዎች አመዘጋገብ ወቅት የሚከሰቱ የመረጃ አደረጃጀትና አያያዝ ችግሮችን በመፍታት ፓርቲዎች በራሳቸው “የሲስተም አስተዳደሪ” አማካኝነት ቢሯቸውን ጨምሮ በተመቻቸው ሥፍራ ያለሰዓት ገደብ በፈቀዳቸው ጊዜ አንዲመዘግቡ ማስቻል፣ እንዲሁም በድምፅ መስጫ ወረቀት ላይ የዕጩዎች አደራደር ቅደም ተከተልን ለመወሠን በሚደረግ የዕጣ አወጣጥ ሥርዓት ወቅት መረጃቸውን እንደ’ አዲስ ማስመዝገብ ሳያስፈልጋቸው ከሲስተሙ ላይ ዕጣውን ማውጣት መቻል ከዋና ዋና ነጥቦች ውስጥ ይጠቀሳሉ።