ቦርዱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በመምረጥ የሚሳተፉበትን ምቹ መደላድል ለመፍጠር ያለመ ውይይት ከተቋማቱ አመራሮች ጋር አደረገ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እና ከትምህርት ሚኒስቴር አመራሮች ጋር የመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተማሪዎች የመራጮች ምዝገባ እና ድምጽ አሰጣጥን በሚመለከት ጥር 19 ቀን 2018 ዓ.ም ውይይት አደረገ፡፡
ውይይቱ የተካሄደው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ ተስፋዬ ንዋይ፣ የዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች፣ የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንቶች እና የትምህርት ሚኒስቴር ተወካይ በተገኙበት ነው፡፡
የውይይቱ ዓላማ ከምርጫ ክልላቸው ርቀው በዩኒቨርሲቲዎች ትምህርታቸውን እየተከታተሉ የሚገኙ ተማሪዎች ልዩ የምርጫ ጣቢያ ተዘጋጅቶላቸው በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የሚሳተፉበትን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ያለመ ነው፡፡
ልዩ የምርጫ ጣቢያ በኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ስነምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 አንቀፅ 17 ንዑስ አንቀፅ (1) እና (4) መሰረት የሚቋቋም የምርጫ ጣቢያ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከምርጫ ክልላቸው ርቀው በካምፕ የሚኖሩ ወታደሮች፣ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚማሩ ዜጎች፣ ከመደበኛ መኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለው በጊዜያዊ መኖሪያ የሚገኙ ዜጎች በምርጫ የሚሳተፉበትን ሁኔታ ለማመቻቸት መራጮቹ በሚገኙበት ቦታ ወይም አካባቢ የሚያቋቁመው የምርጫ ጣቢያ ነው፡፡
የውይይት መድረኩን በንግግር የከፈቱት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ ተስፋዬ ንዋይ የሀገራችን የዴሞክራሲ ሥርዓት እንዲጎለብት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚማሩ ተማሪዎች የመምረጥ መብታቸውን እንዲጠቀሙ ምቹ ሁኔታ ሊፈጠርላቸው እንደሚገባ በአፅንኦት ተናግረዋል፡፡
ለቦርዱ የምርጫ አፈጻጸም የተሻለ የሚሆነው ተማሪዎች በሚማሩበት ተቋም ልዩ የምርጫ ጣቢያ ተደራጅቶላቸው እንዲመዘገቡ ተደርጎ ለምርጫ ወደ ምርጫ ክልላቸው ሄደው ድምጽ እንዲሰጡ ሲደረግ ነው ብለዋል፡፡
በውይይት መድረኩ የተገኙ የተቋማቱ አመራሮች የተለያዩ ጥያቄዎች አንስተው የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ እና የምርጫ ኦፕሬሽን ክፍል ኃላፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በውይይቱ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በምርጫ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት በመራጭነት የተመዘገቡ ተማሪዎች ወደ መደበኛ መኖሪያቸው ተመልሰው የሚመርጡበት ሁኔታ ግንዛቤ ውስጥ የከተተ እንዲሆን የትምህርት ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማቱ ተናበው አስፈላጊውን ማስተካከያ እንዲያደርጉ ተገልጿል::
በመድረኩ ላይ ቦርዱ 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ በስኬት ለማስፈጸም ያከናወናቸው እና በሂደት ላይ ያሉትን የዝግጅት ስራዎች በተለይም በቴክኖሎጂ የተደገፈ የዕጩዎችና መራጮች ምዝገባን በተመለከተ፣ ልዩ የምርጫ ጣቢያዎችን ማቋቋም፣ የምርጫ አስፈጻሚዎችን መመልመል፣ እና ሌሎጅ የዝግጅት ስራዎችን በተመለከተ ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡