ቦርዱ ኅዳር 8 ቀን 2018 ዓ.ም. በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለሚወዳደሩ ፖለቲካ ፓርቲዎች ባስተላለፈው ጥሪ፤ ፖለቲካ ፓርቲዎች “ቦርዱ ያበለጸገውን ሲስተም” ተጠቅመው ዕጩዎቻቸውን ለመመዝገብ እንዲችሉ “በቅድሚያ” ከጥሪው ጋር የተያያዙትን ቅጾች በመጠቀም የተጠየቁትን መረጃዎች አሟልተው ለቦርዱ እንዲያቀርቡ ጥሪ ማስተላለፉ ይታወቃል።
የዕጩ ምዝገባ የሚከናወንበት አግባብ እና የቅጾች አጠቃቀም
1. የፖለቲካ ፓርቲ ቦርዱ ያበለጸገውን የዕጩ መመዝገቢያ ሲስተም ተጠቅሞ ዕጩ ለመመዝገብ በዐዋጅ ቁጥር 1162/2011 እና የዕጩ ምዝገባ መመሪያ መሠረት በቅድሚያ የዕጩ ዝርዝር ማቅረቢያ ቅጽ አምስትን በመጠቀም የዕጩዎችን ዝርዝር መረጃ፤ የፓርቲውን ሊቀ-መንበር ሦስት የፊርማ ናሙና እና የመወዳደሪያ ምልክቱን ለቦርዱ አስቀድሞ ባሳወቀው ወኪል አማካኝነት ከኅዳር 8 እስከ ኅዳር 23 ቀን 2018 ዓ.ም. ለቦርዱ በአካል ማቅረብ ይኖርበታል፡፡
2. ቅጽ አራትን በመጠቀም የፖለቲካ ፓርቲው ከፍ ብሎ በተራ ቁጥር አንድ ላይ የተመለከቱት ሠነዶች በሙሉ የተሟሉ መሆናቸውን በማረጋገጥ እና መጠይቁ ላይ ምልክት በማድረግ ለቦርዱ አስቀድሞ ባሳወቀው ወኪል አማካኝነት ከኅዳር 8 እስከ ኅዳር 23 ቀን 2018 ዓ.ም. ለቦርዱ በአካል ማቅረብ ይኖርበታል፡፡
3. የፖለቲካ ፓርቲው የዕጩ የድጋፍ ፊርማ አሰባሰብ ወጥነት እንዲኖረው ቦርዱ ያዘጋጀውን ቅጽ ሦስትን በመጠቀም መረጃ በማሰባሰብ በዕጩ መመዝገቢያ ሲስተም ላይ የሚጫን ሲሆን፤ ይኽም የሚከናወነው በምርጫው የጊዜ ሠሌዳው መሠረት ቦርዱ ወደፊት በሚያሳውቀው የዕጩዎች የምዝገባ ጊዜ፤ ፓርቲው በወከለው ባለሙያ አማካኝነትና በፖለቲካ ፓርቲው ጽ/ቤት ይሆናል፡፡ >/p>
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ
ኅዳር 10 ቀን 2018 ዓ.ም.