ቦርዱ የ7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ረቂቅ የጊዜ ሠሌዳ አስመልክቶ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ምክክር አደረገ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ በተያዘው ዓመት ለማካሄድ ልዩ ልዩ የቅድመ-ምርጫ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል። ቦርዱ ጥቅምት 10 ቀን 2018 ዓ.ም. የ7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ረቂቅ የጊዜ ሠሌዳ በማስመልከት ከፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና ተወካዮች ጋር ምክክር አድርጓል። ረቂቅ የጊዜ ሠሌዳው የምርጫ ጽ/ቤቶችን ከማደራጀት ጀምሮ እስከ ይፋዊ የምርጫ ውጤት ማሳወቂያ ድረስ ያሉትን ተግባራት ያካተተ ነው።
የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ የምክክር መድረኩን በንግግር ያስጀመሩ ሲሆን፤ በንግግራቸውም የምክክሩ ዐላማ ቦርዱ ያዘጋጀውን ረቂቅ የምርጫ ጊዜ ሠሌዳ በሀገራችን የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ ዋነኛ ተዋናይ የሆኑትን የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና ተወካዮች ሃሳብ እንዲሰጡበት እና የጋራ መግባባት ላይ እንዲደረስ ነው ብለዋል። ሰብሳቢዋ ጨምረውም ፓርቲዎች በምክክሩ መሣተፋቸውና ሃሳባቸውን ማጋራታቸው ለምርጫው ግልጽነት፣ ፍትሐዊነትና፣ ተዓማኒነት ወሣኝ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ቦርዱ በቅድመ ምርጫ ተግባራቱ ያከናወናቸው ዋና ዋና ተግባራት እንዲሁም የምርጫ የጊዜ ሠሌዳው ያካተታቸው ዝርዝር ተግባራት ላይ በቦርዱ የኦፕሬሽን ባለሞያዎች አማካኝነት ገለጻ የተሰጠ ሲሆን፤ ይኽንንም ተከትሎ የመድረኩ ተሣታፊዎች ቦርዱ 7ኛውን ሀገራዊ ምርጫ ከቀደሙት ተከታታይ ምርጫዎች የተሻለ ዴሞክራሲያዊ፣ አሣታፊ እና ግልጽ እንዲሆን ከወዲሁ የጀመራቸው ተግባራት አበረታች ናቸው ሲሉ ገልጸው፤ ረቂቅ የምርጫ ጊዜ ሠሌዳው ታሳቢ ሊያደርጋቸው ይገባል ያሏቸውን ሃሳቦች አቅርበዋል። አያይዘውም የሀገሪቱ የሰላም ሁኔታና የዕጩዎች የድጋፍ ፊርማ ማቅረብን በተመለከተ ስላለው ድንጋጌ ያላቸውን ሥጋት አጋርተዋል።
ከፖለቲካ ፓርቲዎች መሪዎች እና ተወካዮች ለተነሡት ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ የሰጡት የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ፤ ቦርዱ በየአምስት ዓመቱ ምርጫ የማስፈጸም ሕገ-መንግሥታዊ ግዴታው እንደሆነ፤ ይኽም ሲሆን፤ በየተግባራቱ ሁሉ ቅደም ተከተሉን ጠብቆ ከባለድርሻ አካላት ጋር እንደሚወያይና ተጨባጭነት ያላቸውን ሁነቶች ያገናዘበ ውሣኔዎችን እያሳለፈ ግልጸኝነቱን፣ ነፃና ገለልተኛነት እያረጋገጠ ኃላፊነቱን እንደሚወጣ አስታውሰው፤ በቀጣይም የፀጥታ ሁኔታም ሆነ ተያያዥ ጉዳዮችን ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር ፓርቲዎቹን ያሣተፈ ቀጣይ ውይይት እንደሚኖርና ምርጫውን የተመለከቱ ማንኛውም ተግባራት ላይ በቅርበትና በጋራ በመሥራት እንደሚያከናወን ተናግረዋል። ይኽም ሲሆን፤ የፖለቲካ ፓርቲዎችም በበኩላቸው የመራጮችን ትምህርት ጨምሮ የምርጫውን ሰላማዊነትና ዲሞክራሲያዊነት ለማረጋገጥ የሚረዱ ሕጋዊ ተግባራትን ከወዲሁ ዝግጅት በማድረግ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ አሳስበዋል።
ተጨማሪ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶችን ማደራጀት፣ የምርጫ ጣቢያዎችን ዲጂታል በሆነ ሥርዓት መመዝገብ፣ የመራጮችና ዕጩዎችን መመዝገቢያ ቴክኖሎጂ ማበልጸግ፣ ባብዛኛው ክልሎች የመሥክ አሠልጣኞችን መመልመል እና ሌሎችም ቦርዱ በቅድመ-ምርጫ ተግባራቱ እያከናወናቸው ካሉ ተግባራት ውስጥ የሚጠቀሱ ናቸው።