በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ሲደረግ የነበረው የክርክር የተግባር ልምምድ መድረክ ተጠናቀቀ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያዘጋጀውና ከጥቅምት 11 ቀን 2018 ዓ.ም እስከ ጥቅምት 14 ቀን 2018 ዓ.ም ሲካሄድ የነበረው በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የነበረው የክርክር የተግባር ልምምድ መድረክ ተጠናቀቀ። ቦርዱ የ7ኛውን ሀገራዊ ምርጫ ረቂቅ የጊዜ ሠሌዳ ለፖለቲካ ፓርቲዎች ለውይይት ማቅረቡን ተከትሎ መካሄድ የጀመረውና፤ ፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ የክርክር ጊዜ ፖሊሲዎቻቸውንና ፕሮግራማቸውን ለሕዝብ የሚያቀርቡበትን ሥልት እንዲያዳብሩበት ታስቦ የተዘጋጀውን መድረክ የመሩት፤ የሚዲያና የኮሚኒኬሽን ባለሞያ የሆኑት ብሌን ፍጹምና ጌታቸው ድንቁ (ፒ.ኤች.ዲ) ሲሆኑ፤ በእያንዳንዱ ክርክር ማጠቃለያ ላይ ባለሞያዎቹ ተከራካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎቹ የተከተሉት የክርክር ሥነ-ዘዴን ጠንካራና ደካማ ጎን በመለየት ሞያዊ ምክረ ሃሳብ አቅርበዋል።
ተሣታፊ ፖለቲካ ፓርቲዎቹ ባንጻሩ በየዙሩ በነበረው ክርክር ላይ የተከራካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎቹን ጠንካራና ደካማ ጎን ላይ አስተያየት የሰጡ ሲሆን፤ ድምፅ በመስጠይ አሸናፊውን የመለየት ሥራም እንዲሁ ተከናውኗል። አራት ቀን በወሰደው የክርክር መድረክ ማጠቃለያ ላይ ፖለቲካ ፓርቲዎቹ ቦርዱ የክርክር ልምምድ መድረኩን በማዘጋጀቱ ያላቸውን ከፍተኛ አድናቆት ገልጸው፤ ይኽ ተግባር ቀጣይነት ሊኖረው የሚገባና ቦርዱም መሰል ሥራዎችን ለመሥራት የሚያስችለው ድጋፍ እንደሚያስፈልገው ተናግረዋል።
የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ሜላት ወርቅ ኃይሉ በመድረኩ ማጠቃለያ ንግግራቸው ተሣታፊ ፖለቲካ ፓርቲዎችን አመስግነው፤ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ የክርክር ዐቅም በተለያየ መንገድ የተገለጠ መሆኑን ገልጸው ያመሰገኑ ሲሆን፤ ፓርቲዎቹ ቦርዱ ከሚያደርገው ጥረት በተጨማሪ ከምርጫው በፊት የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም የክርክር ልምዳቸውን ማዳበር እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል። ይኽውም ምርጫ በአምስት ዓመት አንዴ የሚገኝ ሁነት እንደመሆኑ መጠን አጋጣሚውን ውጤታማ በመሆን ለመጠቀም እንደሚረዳ ገልጸዋል። በመጨረሻም ድጋፍ ላደረገው የNetherlands Institute for Multiparty Democracy (NIMD) እና መድረኩን ለመሩት ባለሞያዎች ምስጋናቸውን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር ዐዋጅ 1162/2011 ለፓርቲዎች (ለዕጩዎች) በመንግሥት የመገናኛ ብዙኃን ነፃ የዐየር ጊዜ አግኝተው ፖሊሲዎቻቸውንና ፕሮግራማቸውን እንዲያስተዋውቁ ከሚደነግገው በተጨማሪ፤ የፓርቲዎች የክርክር መድረክ ሌላኛው የፖሊሲና የፕሮግራም ማስተዋወቂያ አማራጭ ነው።