Skip to main content

ቦርዱ የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ረቂቅ የምርጫ ጊዜ ሠሌዳውን በተመለከተ ከመገናኛ ብዙኃን እና ከሲቪል ማኀበረሰብ ድርጅቶች ጋር ምክክር አደረገ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ረቂቅ የምርጫ ጊዜ ሠሌዳን በተመለከተ ከመገናኛ ብዙኃን እና ከሲቪል ማኀበረሰብ ድርጅቶች ጋር በትላንትናው ዕለት ጥቅምት 17 ቀን 2018 ዓ.ም. ምክክር አደረገ። አምስትቱም የቦርድ አመራር አባላት የተገኙበትን መድረክ በንግግር የከፈቱት የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ ሲሆኑ፤ በንግግራቸውም ባሳለፍነው ሣምንት ቦርዱ በረቂቅ የጊዜ ሠሌዳው ላይ ከፖለቲካ ፓርቲዎችና በመራጮች ቅስቀሳ ላይ ከተሠማሩት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጋር እንደየቅደም ተከተላቸው እንደመከረና ለሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶቹ የዕውቅና የምሥክር ወረቀት እንደሰጠ፤ በዚኽኛው የምክክር መድረክም በተመሳሳይ ከመገናኛ ብዙኃን ተወካዮችና የመራጮች ትምህርት ላይ እንዲሁም በመታዘብ ላይ ከሚሣተፉ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮች ጋር በመወያየት አሠሪ የጊዜ ሠሌዳ ይፋ እንደሚደረግ ተናግረዋል። አያይዘውም ቦርዱ በየተግባራቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተወያየ ውሣኔዎችን በማሳለፍ የምርጫውን ነፃ፣ ፍትሐዊና አሣታፊነት እያረጋገጠ እንደሚቀጥል አጽንዖት ሰጥተዋል።

የሰብሳቢዋን ንግግር ተከትሎ የቦርዱ የኦፕሬሽን ሥራ ክፍል ኃላፊ በሆኑት ብሩክ ወንድወሠን አማካኝነት ቦርዱ በቅድመ ምርጫ ተግባራቱ ስላከናወናቸው ተግባራትና የጊዜ ሠሌዳው ታሳቢ ስላደረጋቸው ዝርዝር ተግባራት ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፤ ተሣታፊዎቹም እንዲሁ የጊዜ ሠሌዳው ታሳቢ ሊያደርጋቸው ይገባል ያሏቸውንና አጠቃላይ ምርጫው ስኬታማ እንዲሆን ከወዲሁ መሠራት ስላለባቸው ተግባራት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። በዚኽም ቦርዱ ከወዲሁ ባለድርሻ አካላትን እያወያየ ውሣኔ ለማሳለፍ ያሳየውን ቁርጠኛነት፣ ቀደም ሲል ቦርዱ በቴክኖሎጂ የታገዘው “ራስ-አገዝ” የመመዝገቢያ መተግበሪያውን በማበልጸግ ሂደት የአካል ጉዳተኞች በተለይም የዓይነ ሥውራን ማኅበራትን በመጋበዝ አስተያየት እንዲሰጡበት ማስደረጉን፣ የመገናኛ ብዙኃን አካላትንም እንዲሁ የጊዜ ሠሌዳውን በማስተቸት ሂደቱ ማሣተፉ የሚደነቅ መሆኑን፣ የመራጮች ትምህርት ያለመቋረጥ መሰጠት ስላለበት አግባብ፣ እንዲሁም ስለፀጥታ ጉዳይና ሌሎች ተያያዝ ጉዳዮች ላይ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ተሣታፊዎቹ ላነሧቸው ጥያቄዎችና አስተያየቶች ሜላትወርቅ ምላሽ የሰጡ ሲሆን፤ የመራጮች ትምህርት በጊዜ ሠሌዳው ላይ በልዩ ሁኔታ የተቀመጠባቸው ቦታዎች ትምህርቱ እጅግ አስፈላጊ የሚሆንባቸውን ጊዜያት ለማመላከት መሆኑን፣ ነገር ግን ትምህርቱ የማይቋረጥና ቀጣይነት ያለው መሆን እንደሚገባው በዚኽም የሲቪል ማኅበራቱ ብቻ ሣይሆን የመገናኛ ብዙኃን አካላት ተሣትፎ ትልቅ ሚና ሊኖረው እንደሚገባ፣ ቦርዱ ቴክኖሎጂን ጥቅም ላይ የሚያውለው በመራጮችና ዕጩዎች ምዝገባ ላይ ብቻ መሆኑንና የድምፅ መስጠቱ ሂደት ግን ከዚኽ በፊት በነበረው መደበኛ ሥርዓት እንደሚቀጥል፤ ይኽም ሲሆን በቴክኖሎጂ ከታገዘው የመራጮች ምዝግባ ጎን ለጎን መደበኛው የመራጮች ምዝገባ ሥርዓትን ብቻ የሚያከናውኑ የምርጫ ጣቢያዎች እንደሚኖሩ ተናግረዋል። የፀጥታ ጉዳይን በተመለከተ ሲናገሩም፤ ቦርዱ አሁናዊ የፀጥታ ሁኔታዎችን ከሚመለከታቸው የመንግሥትና ከባለድርሻ አካላት መረጃ በመሰብሰብና በመምከር ተጨባጭና አሁናዊ የፀጥታ ሁኔታዎች ላይ አሣታፊ የሆነ የክትትልና የቁጥጥር ቡድን በማሠማራት የሁኔታዎች ትንተና እንደሚሠራ ገልጸዋል። ቦርዱ ተጨማሪ የክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች መክፈቱም የምርጫ ሥራውን ቅልጥፍና እንዲሚያግዝና ተደራሽ ለመሆንም እንደሚያስችል ተናግረዋል።

ቦርዱ በትላንትናው ዕለት ጥቅምት 17 ቀን 2018 ዓ.ም. የምርጫ ክልል አስፈጻሚ ለመሆን ፍላጎት ላላቸው አመልካቾች ይፋዊ የምዝገባ ጥሪ አድርጓል።

Share this post