Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተለያዩ ሀገራት አቻ የምርጫ አስፈጻሚ ተቋማትን እና የ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ መልካም ተሞክሮዎችን የተመለከተ ልዩ መርኃ-ግብር አካሄደ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተለያዩ ሀገራት አቻ የምርጫ አስፈጻሚ ተቋማትን እና የ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ መልካም ተሞክሮዎችን የተመለከተ ልዩ መርኃ-ግብር አካሄደ። አምስቱም የቦርድ አመራር አባላት፣ የየሥራ ክፍልና የክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊዎች እንዲሁም ከፍተኛ ባለሞያዎች በተሣተፉበት መድረክ ላይ፤ የተለያዩ ሀገራትን ምርጫዎች በመታዘብ ወቅት የተገኙ ልምዶችን እንዲሁም ከምርጫ አስፈጻሚ ተቋማት ጋር በተደረጉ የአቻ-ላቻ ልምድ ልውውጦች የተገኙ መልካም ተሞክሮዎችን በተመለከተ በሁነቶቹ ላይ ተሣታፊ በነበሩ የቦርዱ ባለሞያዎች አማካኝነት ገለጻ ተሰጥቷል። በተወካዮቹ የቀረቡትን መልካም ተሞክሮዎች ተከትሎ በቡድን በቡድን በመሆን ከሀገራቱ ተሞክሮዎች ውስጥ ለኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ተስማሚና ተፈጻሚ መሆን የሚችሉት የትኞቹ ናቸው የሚሉት ላይ በመወያየት ሃሳብ የቀረበ ሲሆን፤ የ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ መልካም ተሞክሮዎችን በተመለከተም እንዲሁ አጭር ዘጋቢ ፊልም በማሳየት፤ ነባር የቦርዱ ባለሞያዎች ሊወሰዱ ይገባል ስላሏቸው መልካም ተሞክሮዎች ሃሳብ ሰጥተዋል።

ባሳለፍነው ሣምንት ለተከታታይ ሦስት ቀናት በተካሄደው መድረክ ላይ ከላይ ከተጠቀሱት አጀንዳዎች በተጨማሪ የምርጫ ሥራን ያገናዘበ ሥነ-ተግባቦትን፣ የግጭት አፈታትን፣ “የጭንቀት” ዓይነቶች እንዲሁም ምልክቶቹን፣ መንስዔዎችን እና ጭንቀትን እንዴት መቆጣጠርና ማስተዳደር እንደሚቻል፣ በተጨማሪም ለተሰጠ ኃላፊነት ሊኖር ስለሚገባው ተጠያቂነት እንዲሁም ኃላፊነትን በመፈጸም ሂደት ሊከበሩ የሚገቡ የሥልጣን ተዋረድን ጠብቆ የመሥራት ሥነ-ሥርዓቶችን አስመልክቶ ሳይንሳዊ ገለጻዎች የተሰጡ ሲሆን፤ በቡድን በመሆንም ተሣታፊዎቹ እንዲወያዩባቸውና ሃሳብ እንዲሰጡባቸው ተደርጓል።

የ2017 ዓ.ም. በጀት ዓመት አፈጻጸምም ከተለምዷዊ አቀራረብ በተለየ መልኩ ሁሉም ሥራ ክፍሎች ሥኬቶቻቸውንና ያጋጠሟቸው ተግዳሮቶችን በባዛር መልኩ ለተሣታፊዎች እንዲያቀርቡ በማድረግ ውይይት የተደረገበት ሲሆን፤ የተያዘው በጀት ዓመት ቀሪ አፈጻጸምና የመጪው ምርጫ ሥራዎች በቦርዱ በተዘጋጀው የስትራቴጂክ ዕቅድ መሠረት የተቃኙ መሆን እንደሚገባ አስተያየት ተሰጥቶበታል። የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ በመድረኩ የማጠቃለያ ንግግራቸው፤ የመድረኩ አዘጋጅ ኮሚቴዎችንና ልምዳቸውን ያካፈሉ ባለሞያዎችን ያመሰገኑ ሲሆን፤ የመድረኩ ተሣታፊዎች እንደየሥራቸው ባህሪያት ከተለያዩ ሀገራት እና ከ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ የተገኙ ልምዶችን፤ በቀጣዩ 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ላይ ተፈጻሚ ማድረግ በሚያስችል መልኩ በሥራቸው ላሉ ባለሞያዎች ማጋራት እንደሚገባ በአፅንዖት ተናግረዋል። በመጨረሻም ድጋፍ ላደረገው European Centre for Electoral Support (ECES) ምስጋናቸውን ገልጸዋል።

Share this post