ቦርዱ በምርጫ መታዘብ ላይ ለሚሣተፉ የሲቪል ማኀበረሰብ ድርጅቶች የምርጫ መታዘብ ሥነ-ዘዴን የተመለከተ ሥልጠና ሰጠ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 7ኛውን ሀገራዊ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችለውን በርካታ የቅድመ-ዝግጅቶች ሥራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል። ከነዚኸም ውስጥ መራጮች እና ዕጩዎችን በቴክኖሎጂ በመታገዝ እንዲመዘገቡ የሚያስችል ሥርዓት መዘርጋት በዋናነት ተጠቃሽ ሲሆን፤ ይኽን እና መሰል ተግባራትን ሲያከናውንም የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን ጨምሮ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀራርቦ በመሥራት ነው።
ቦርዱ በምርጫ መታዘብ ላይ ለሚሠማሩ የሲቪል ማኀበረሰብ ድርጅቶች የምርጫ መታዘብ ዕቅድ ዝግጅት እና የግኝት ሪፖርት አቀራረብ ሥነ-ዘዴ ላይ ያተኮረ ሥልጠና በትላንትናው ከትላንት በስትያ ጥቅምት 4 ቀን 2018 ዓ.ም. ሰጠ።
የሥልጠናውን የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ በንግግራቸው፤ ምርጫ ነፃና ፍትሐዊ እንዲሆን፣ ዜጎች በነቂስ ወጥተው በምርጫው ተሣታፊ እንዲሆኑ፣ እንዲሁም በዲሞክራሲያዊ ምርጫ ተመርጦ መንግሥት የሚሆነው አካል ቅቡልነት እንዲያገኝ ገለልተኛ የሲቪል ማኀበረሰብ ድርጅቶች ሚና የማይተካ እንደሆነ አስረድተዋል። በተለይም በምርጫ ታዛቢነት ላይ የሚሠሩ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የታዛቢነት ስራን ነፃ፣ ገለልተኛና አካታችነትን ባማከለ መልኩ መከወን ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል። የተሻሻሉ የሕግ ማዕቀፎች፣ ሴቶች እና አካል ጉዳተኞች በመታዘብ ሂዳት ላይ ስለሚካተቱበት አግባብ፣ የምርጫ መታዘብ መርኆዎች እና ሳይንሳዊ የመረጃ አሰባሰብ ሥነ-ዘዴ በሥልጠናው ከተካተቱ ርዕሰ-ጉዳዮች ውስጥ ይጠቀሳሉ።
በሥልጠናው ላይ የተሣተፉ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በበኩላቸው ቦርዱ ከ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ልምድ በመውሰድ የምርጫ ታዛቢዎችን ከወዲሁ ማሠልጠኑ የሚደነቅ እንደሆነ በመግለጽ፤ ይህ ሥልጠና የምርጫው ቀን ሲቃረብ የሚከሰቱ በተለይም የምርጫውን ተዓማኒነት ጥያቄ ውስጥ የሚያስገቡ ጉዳዮችን ከወዲሁ መልስ ለመስጠት እንደሚረዳ ያላቸውን ዕምነት ገልጸዋል።
ከሠልጣኞች ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት ሜላትወርቅ፤ የምርጫ ታዛቢዎች በመረጡት ቦታ የመታዘብ መብት እንዳላቸው፤ ቦርዱም እንዲሁ ሁኔታዎችን ምቹ የማድረግ ኃላፊነት እንዳለበት ገልጸዋል። የምርጫ ታዛቢዎች እርስ በርስ በመናበብና በመነጋገር በተመሳሳይ ቦታዎች ብቻ በመታዘብ ሳይወሠኑ የትኛው ታዛቢ በየትኛው አካባቢ ይታዘባል የሚለው ላይ አስቀድሞ በመወያየት ተደራሽነትን የማረጋጋጥ ሥራ መሥራት እንዳለባቸው አጽንዖት ሰጥተው አሳስበዋል፡፡

