የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በ21ኛው ዓለም ዐቀፍ የምርጫ ቦርድ ተቋማት ሲምፖዚየም ሽልማት ተሸላሚ ሆነ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በቦትስዋና በተካሄደው በ21ኛው ዓለም ዐቀፍ የምርጫ ቦርድ ተቋማት ሲምፖዚየም ሽልማት የ Electoral Ergonomic Award Recognition for Outstanding Achievement ተሸላሚ ሆነ። ከመስከረም 22-23 ቀን 2018 ዓ.ም. የተካሄደውን ሲምፖዚየም Independent Electoral Commission of Botswana ከ International Centre for Parliamentary Studies (ICPS) ከተባለው ዓለም ዐቀፍ ተቋም ጋር በመተባበር ያዘጋጁት የዲሞክራሲያዊ ልኅቀት ማጎልበቻና የልምድ ልውውጥ ማድረጊያ ሲምፖዚየም ሲሆን፤ የተለያዩ ክፍላተ-ዓለም ሀገራት የምርጫ ቦርድ ተቋማት ኮሚሽነሮች ተሣትፈውበታል።
ሽልማቱ ቀጣዩ 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ አካታች፣ ተደራሽ፣ ተዓማኒ፣ ግልጽ እንዲሆን የቦርዱ ሠራተኞች እያደረጉ ያለውን መርኅ ላይ የተመሠረተ እንዲሁም የመራጩን ሕዝብ ግንዛቤ ማሳደግን ያማከለ ሁለንተናዊ ትጋት ዕውቅና በመስጠት ነው፡፡ በሌላም በኩል የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላት ወርቅ ኃይሉ “From Access to Influence: Making Elections Truly Inclusive” በሚለው ርዕስ ላይ በፓናሊስትነት የተሳተፉ ሲሆን፤ ምርጫ ተደራሽ ብቻ ሳይሆን ከምርጫ በኋላ ውጤቱ በህግና ፖሊሲ ላይ ተፅዕኖ ሊፈጥር እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡ ይህንን ለማረጋገጥ ሁሉም ባለድርሻ አካላት፤ የምርጫ አስፈፃሚ አካላት (EMBs)፣ የሲቪክ ማህበረሠብ ድርጅቶች፣ ተመራጮች (Electoral officials)፣ መንግስት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የምርምር ተቋማት እና የመገናኛ ብዙሃን ኃላፊነት እንዳለባቸው ገልፀዋል፡፡
በተጨማሪም በሲምፖዚየሙ ላይ አምና የተካሄደው የቦትስዋና ምርጫ፤ ሀገሪቱ ከቅኝ አገዛዝ ነፃ ከወጣችበት ጊዜ ጀምሮ ካከናወነቻቸው ምርጫዎች ሁሉ በፖለቲካ ፓርቲዎች መኻል ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር በማስተናገድ ረገድ ትልቅ ውጤት ማስመዝገቡ ዕውቅና ተሰጥቶበታል። በምርጫው ላይ ከፍተኛ የመራጮች ቁጥር የታየበት ሲሆን፤ ይኽም ከሀገሪቱ ሕዝብ 80% ተሣትፈውበታል።
አሜሪካ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ናሚቢያ፣ ጆርጂያ፣ ሴራሊዮን፣ ፊሊፒን፣ ዝምባብዌ፣ በዩኖስ አይሬስ፣ ሕንድ፣ ሜክሲኮ፣ አርጀንቲ፣ ኡታራካንድ እና ፔሩ በምርጫ ተቋማታቸው አማካኝነት ከተሣተፉ ሀገራት ውስጥ ይጠቀሳለሉ። በተጨማሪም ከተለያዩ ሀገራት የመጡ ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ተቋማት፣ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት፣ እንዲሁም የምርጫ ጉዳይ ለጋሽ ተቋማት በሲምፖዚየሙ ላይ ተሣታፊ ሆነዋል።


