የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሴት ፖለቲከኞች በ7 ኛው ሀገራዊ ምርጫ የሚኖራቸውን ተሣትፎ ለማሳደግ የሚያስችል የዐቅም ግንባታ ሥልጠና ሠጠ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተቋማዊ ኃላፊነቱን ሲወጣ ትኩረት ከሚሰጣቸው ተግባራት አንዱ የሥርዓተ-ፆታና ማኅበራዊ አካታችነት ተጠቃሽ ነው። ቦርዱ ሴት ፖለቲከኞች በ7 ኛው ሀገራዊ ምርጫ የሚኖራቸውን ተሣትፎ ለማሳደግ በማሰብ መስከረም 19-20 ቀን 2018 ዓ.ም. የዐቅም ግንባታ ሥልጠና ሠጠ፡፡ የመድረኩን መክፈቻ ንግግር የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ ያደረጉ ሲሆን፤ በንግግራቸውም ቦርዱ ሴቶችና እና አካል ጉዳተኞች በምርጫ ላይ የነቃ ተሣትፎና የጎላ ድርሻ እንዲኖራቸው የሚያበረታቱ ድንጋጌዎች በሕግ-ማዕቀፎቹ እንዲካተቱ ከማድረግ ባሻገር፤ በርካታ የዐቅም ግንባታ ሥልጠናዎችንና ድጋፎችን እየሰጠ እንደሚገኝ አስታውሰው፤ ይህም ሥልጠና በ7 ኛው ሀገራዊ ምርጫ የነቃ ተሣትፎ እንዲኖራቸው እንደሚያስችል ያላቸውን ዕምንት ገልጸዋል።
የሥልጠና ተሣታፊዎች የፓርቲዎቻቸውን ፕሮግራምና አሠራር በመፈተሸ አካታችነት ላይ በትኩረት መሥራት እንዳለባቸው ያሳሰቡት ሰብሳቢዋ፤ ሥልጠናው የሴቶችና የአካል ጉዳተኛ ፖለቲከኞችን የምርጫ ተሣትፎ ከማጎልበትም በላይ የሚገጥሟቸውን ውጫዊ እና ውስጣዊ ተግዳሮቶችና መፍትሄዎቻቸው ላይ ግንዛቤ ለመፍጠር ብሎም በሴቶች በጥምረት እና ክንፎች መካከል አብሮ የማቀድና የመሥራት ባህል እንዲኖር ያግዛል ብለዋል።
የሴት ፖለቲከኞች መብቶችና አስቻይ የሕግ-ማዕቀፎች፣ የፖለቲካ ኃይል ምንጭና አጠቃቀም፣ የፖለቲካ ተቋማት ባህሪና የሥርዓተ ፆታ አካታችነትን ያማከለ ተቋም መገለጫዎችን በተመለከተ ግንዛቤ ማስጨበጥ ዐላማውን ባደረገው መድረክ ላይ በኢትዮጵያ ፓለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሥር ያሉ የሴቶች፣ የአካልጉዳተኛ እንዲሁም የወጣቶች ክንፍ እና የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲ ሴት አባላት ጥምረት አባላት የተሣተፉ ሲሆን፤ ሥልጠናውም የዘርፉ ባለሞያ በሆኑት ዶ/ር ጥሩዬ ዓለሙ አማካኝነት ተሰጥቷል።
ተሣታፊዎቹ ከላይ በተጠቀሱት አጀንዳዎች ዙሪያ በቡድን ተከፋፍለው የተወያዩና የውይይታቸውንም ፍሬ ሃሳብ ያቀረቡ ሲሆን፤ ከሥልጠናው ያገኙትንም ግንዛቤ በተዋረድ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ እንደሚሠሩ ቃል ገብተዋል። በሥልጠናው ማጠቃለያ ላይ ከተሣታፊዎች ለተነሡት ጥያቄዎች የቦርድ አመራር አባሏ ነሲም ዓሊ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፤ ለሥልጠናው የቴክኒክ ድጋፍ ላደረገው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሥርዓተፆታ ዕኩልነትና ሴቶችን የማብቃት ክፍል ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

