ቦርዱ ዲጂታል የመራጮችና የዕጩዎች ምዝገባ ረቂቅ መመሪያዎች ላይ ከፓለቲካ ፖርቲዎች እንዲሁም ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጋር ተወያየ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በተያዘው ዓመት በሚያካሂደው 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ከሚያስተዋውቃቸው ዘመናዊ የምርጫ ሥርዓት ውስጥ አንዱ መራጮችና ዕጩዎች ኢንፍራስትራክቸር ባሉባቸው ቦታዎች በመሆን ራሳቸውን በራሳቸው በመራጭነት አልያም በዕጩነት እንዲመዘግቡ የሚያስችል የዲጂታል አማራጮች እንደሆኑ ይታወቃል። ቀደም ሲል ቦርዱ ያበለጸገውን በቴክኖሎጂ የታገዘ የመመዝገቢያ ሥርዓት ምን ዓይነት ሂደትን እንደሚከተል የአተገባበር ቅደም ተከተሉን ለፖለቲካ ፓርቲዎችና ለሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮች በማሳየት ግብዓት የሰበሰበ ሲሆን፤ ሥራውን ለመሥራት የሚያስችለውን የተሻሻለውን ዐዋጅ ተከትሎም መመሪያ ማውጣት በማስፈለጉ ባሳለፍነው ሣምንት መስከረም 9 እና 10 ቀን 2018 ዓ.ም. ከፓለቲካ ፖርቲ ተወካዮች እንዲሁም ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮች ጋር አምስቱም የቦርድ አመራር አባላት በተገኙበት ምክረ-ሐሳብ መሰብሰቢያ ውይይት አኳሂዷል።
የውይይቱን የመክፈቻ ንግግር የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ ያደረጉ ሲሆን፤ በንግግራቸውም የምርጫ ቴክኖሎጂ ሰፊና መልከ ብዙ መሆኑን አስታውሰው፤ አሁን ላይ ቦርዱ የሚተገብረው የምርጫ ቴክኖሎጂ መሠረታዊ በሆነው መራጮችንና ዕጩዎችን በመመዝገብ ብቻ የተወሠነ እንደሆነና ድምፅ የመስጠት ሂደት፤ ቆጠራና የውጤት ማሳወቂያ ሥራዎች ግን ቀደም ሲል በነበረው የአሠራር ሥርዓት እንደሚቀጥል ተናግረዋል። ቦርዱ ያበለጸገው የምዝገባ ቴክኖሎጂ መራጮችና ዕጩዎች በጊዜ ማጣት፣ በቦታ ርቀት እንዲሁም በተለያዩ ምክንያቶች መመዝገብ እየፈለጉ ሳይመዘገቡ የሚቀርበትን አጋጣሚ በማስቀረት እንዳይጉላሉ ከማድረግ በተጨማሪ የተረጋገጠ መረጃዎችን ለማደራጀትም ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
የሰብሳቢዋን ንግግር ተከትሎ የሕግ ባለሞያ የሆኑት ኒቆዲሞስ ጌታሁን እና ጌዲዮን ሲሳይ ረቂቅ መመሪያዎቹ ላይ የተደነገጉትን ዝርዝር አንቀጾች ላይ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፤ በማስከተልም ተሣታፊዎቹ በቡድን በቡድን በመሆን ረቂቅ መመሪያዎቹ ላይ በመወያየት ገንቡ ያሏቸውን አስተያየቶች ሰጥተዋል።
በውይይቱ የመዝጊያ ንግግራቸው የቦርዱ ሰብሳቢ ተሣታፊዎቹ ለሰጡት ግብዓት አመስግነው ቦርዱ ከዐዋጁ ጋር የሚጣጣሙትን አስተያየቶች በሙሉ እንደሚወስዳቸው ተናግረው፤ ረቂቅ ደንቡን በማዘጋጀት ተሣትፎ ላደረጉ ባለሞያዎች አድናቆታቸውን ገልጸዋል። ቦርዱ ኢንፍራስትራክቸሩ ተደራሽ ባልሆነባቸው አካባቢዎች ቀደም ሲል በነበረው ሥርዓት የሚመዘግብ ይሆናል።

































