Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለሥነ-ዜጋ እና ለመራጮች ትምህርት ክፍል ባለሙያዎቹ የዐቅም ግንባታ ሥልጠና ሰጠ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፤ በ2018 የሚያስፈጽመው 7ኛው ሀገራዊ ምርጫን አስመልክቶ እያከናወናቸው ከሚገኙ በርካታ ተግባራት ውስጥ የቦርዱን ባለሞያዎች ዐቅም የሚያጎለብቱ ሥልጠናዎችን መስጠት ይጠቀሳል። ቦርዱ ነሐሴ 28-29 ቀን 2017 ዓ.ም. ለዋናው መሥሪያ ቤትና ለቅርንጫፍ ጽ/ቤቶቹ የሥነ-ዜጋ እና የመራጮች ትምህረት ሥራ ክፍል ባለሞያዎቹ ሥልጠና ሰጠ። የሥልጠናውን የመክፈቻ ንግግር የቦርድ አመራር አባል የሆኑት ተክሊት ይመስል ያደረጉ ሲሆኑ፤ በንግግራቸውም የሥልጣን ባለቤት ሕዝብ መሆኑን አስታውሰው የመራጮች ትምህርት መስጠቱም፤ የሥልጣን ባለቤት የሆነው ሕዝብ አስፈላጊው ግንዛቤ ኖሮት እንዲመርጥ እንደሚያስችለው ተናግረዋል። ይኽም ሲሆን በሥልጠናዎቹ አካታች መሆን መሠረታዊ ነገርና የግድ የሚል እንደሆነ አስገንዝበዋል።

ቦርዱ ቀደም ሲል ዜጎች በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ምርጫን እንዲያደርጉ የሚያግዙ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን ሲሠራ የቆየ ሲሆን፤ ከዚህም ጋር በተያያዘ ቦርዱ የተለዩ የምርጫ ዘመቻዎችንና የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራዎችን ወደ ማኅበረሰቡ ተደራሽ በማድረግ ሥራ ላይ ቀዳሚና ከፍተኛ ተሣትፎ ላላቸው የቦርዱ የዋና መሥሪያ ቤትና የክልል ቅ/ጽ/ቤት የሥነ ዜጋ እና የመራⶐች ትምህርት ክፍል ባለሙያዎች የሁለት ቀናት የዐቅም ግንባታ ሥልጠና ሰጥቷል።

የንግግር ክኅሎት፣ የሕዝባዊ መድረክ ማስተባበር፣ ብቁ አመራርነት፣ የምርጫ ዑደት፣ የግጭት አፈታት ሥነ-ዘዴ ሥልጠናው ካካተታቸው ዐጀንዳዎች ውስጥ ይጠቀሳሉ። የዐቅም ግንባታ ሥልጠናው በቦርዱ ዋና መሥሪያ ቤት የሥነ-ዜጋ እና መራጮች ትምህርት ክፍል ባለሙያዎች ከEuropean Center for Electoral Support (ECES) የሥልጠና ባለሙያዎች ጋር በመተባበር ተሰጥቷል። ECES በተጨማሪም የቴክኒክ ድጋፍ አድርጓል።

Share this post