Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለቀድሞ የቦርዱ ሥራ አመራሮች የምስጋና ሽኝት እንዲሁም ለአዲስ ተሿሚዎች የእንኳን ደኽና መጣችሁ መርኅ-ግብር አካሄደ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን ላለፉት ስድስት ዓመታት ያገለገሉት የቀድሞ የቦርድ ሥራ አመራር አባላት፤ ምክትል ሰብሳቢ ውብሸት አየለ፣ የቦርድ ሥራ አመራር አባላት ብዙወርቅ ከተተ እና ዶ/ር አበራ ደገፋ የምስጋና ሽኝት ሥነ-ሥርዓት፤ እንዲሁም የአዲስ ተሿሚ ሥራ አመራር አባላት፤ ምክትል ሰብሳቢ ተስፋዬ ነዋይ፣ የቦርድ ሥራ አመራር አባላት ተክሊት ይመስል እና ነሲም አሊን የአቀባበል ሥነ-ሥርዓት ተካሂዷል።

የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ እና የቦርድ ሥራ አመራር አባሉ ፍቅሬ ገ/ሕይወት፣ የቀድሞ የቦርድ ሥራ አመራር አባላት ቤተሰቦች፣ የቦርዱ የዋናውና የቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሠራተኞች እንዲሁም ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት የተካሄደው የምስጋና ሽኝት መድረክ ላይ በርካታ የቀድሞ ሥራ አመራሮችን ስኬት የሚያሳዩ አጫጭር ዶክመንተሪዎች የታዩ ሲሆን፤ በቦርዱና በሥራ ባልደረቦቻቸውም የአክብሮትና የምስጋና መግለጫ ሽልማቶች ለቀድሞ አመራሮችና ለቤተሰቦቻቸው ተበርክቷል።

የቀድሞ የቦርድ ሥራ አመራር አባላትን ያካተተው አመራር ሰጪነት በስድስት ዓመት የአመራርነት ዘመኑ ምን አሳካ?

አንድ ሀገራዊ ምርጫና ሦስት ሕዝበ-ውሣኔዎችን ማስፈጸም፣ ቦርዱን በገለልተኛና በብቁ ባለሞያዎች እንዲደራጅ ማድረግ፣ የቦርዱ ባለሞያዎች በሀገር ውስጥና በውጪ ሀገራት የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን እንዲወስዱ ማስቻል፣ ሥርዓተ-ፆታና ማኅበራዊ አካታችነትን ከግምት ውስጥ ያስገባ 26 መመሪያዎችና በርካታ ማንዋሎችን ማርቀቅ፣ በርካታ ጥናቶች በተለይም በሥርዓተ ፆታና ማኅበራዊ አካታችነት ዙሪያ እንዲደረግ አመራር መስጠት፣ የቦርዱን የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ ማጽደቅ፣ በቦርዱ ቀጥተኛ ድጋፍ የሚደረግለት የፓለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት እንዲቋቋም ማድረግ፣ በ12ቱም ክልሎች እንዲሁም በሁለቱ ከተማ መስተዳድሮች የሥነ-ዜጋና የመራጮች ትምህርት ላይ ግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናዎች እንዲሰጡ ማመቻቸት፣ የሦስትዮሽ ኮሚቴ በማቋቋም የታሠሩ የፖለቲካ ፖርቲ አመራሮችና አባላት እንዲፈቱ ማስተባበር፣ በተመረጡ ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ ፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲወያዩ ማድረግ፣ የምርጫ አስፈጻሚዎች የምልመላ ሂደት የፓለቲካ ፓርቲዎችን ባሣተፈ መልኩ ተፈጻሚ የሚሆንበትን የአሠራር ሥርዓት መዘርጋት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሴት አባላት ጥምረት እንዲቋቋም ማድረግ፣ ምርጫ ጣቢያዎቹ የሚገኙበትን ትክክለኛ ቦታዎች የGIS ቴክኖሎጂን በመጠቀም በ‘’XY Coordinate’’ የመለየት እና የመመዝገብ ሥራ እንዲሠራ አመራር መስጠት፣ በቴክኖሎጂ የታገዘ የዕጩዎችና የመራጮች ምዝገባ ሥርዓት እንዲበለጽግ ማስቻል፣ በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ለአፈጻጸም አስቸጋሪ የነበሩ ደንቦችን የያዘውን የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር ዐዋጅ 1162/2011ን እንዲሻሻል በማድረግ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መምራት፣የክልሎችንና የከተማ መስተዳድሮችን የሕዝብ ቁጥርና መልከዓ-ምድራዊ አቀማመጥ ከግምት ውስጥ ያስገባ ተጨማሪ የክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች እንዲከፈቱ ማድረግ ተጠቃሽ ናቸው።

በመድረኩ ላይ የቀድሞ የቦርድ ሥራ አመራሮችና አዲስ ተሿሚ አመራሮች በቦርዱ ዋና ሰብሳቢ አማካኝነት ይፋዊ የሥራ ርክክብ ማድረጋቸውን የቦርዱን ዐዋጅ በመቀባበል ያሳዩ ሲሆን፤ ይኽንንም ተከትሎ ተሿሚ አመራሮቹ ከፍተኛ ኃላፊነት መሆኑን አስታውሰው ለቀድሞ የቦርድ ሥራ አመራር አባላት ስለአገልግሎታቸው ያላቸውን አድናቆትና ምስጋና ገልጸው፤ የቦርዱን ነፃነት እና ገለልተኛነት አስጠብቀው ከቦርዱ አመራሮችና ባለሞያዎች ጋር በመሆን የተቋም ግንባታና የተሻለ የምርጫ ሥርዓትን የመፍጠር ሂደቱን የሚያረጋገጥ ሥራ እንደሚሠሩ ቃል ገብተዋል።

በሥነ-ሥርዓቱ ማጠቃለያ ላይ አዲስ ተሿሚ የቦርዱ ሥራ አመራር አባላት በየተራ ባደረጉት ንግግር፤ የቦርዱን ተቋማዊ ቁመናና ገለልተኛ የሥራ አፈጻጸም በውጭ ሆነው ሲያደንቁት የነበረ መሆኑን ጠቅሰው፤ በቦርድ ሥራ አመራርነት ከቀናት በፊት ቢሮም ገብተው ያዩት ነገር ውጪ ሆነው የታዘቡትን የሚያጠናክርና የቦርዱንም ባለሞያዎች "Team spirit" በተጨባጭ ዐይተው የተደነቁበት መሆኑን ገልፀዋል። የቦርዱ ሰብሳቢ በርክክቡ ወቅት ባደረጉት ንግግር፤ ለቀድሞ የቦርድ ሥራ አመራር አባላት ያላቸውን አድናቆት በቦርዱ ላይ ያኖሩትን አሻራ በማስታወስ ጭምር የገለጹ ሲሆን፤ የዲሞክራሲ አንዱ መገለጫ ኃላፊነትን የመረካከብ ሂደት መሆኑን አስታውሰው፤ ቀሪ የቦርድ አመራር አባላትና አዲስ ተሿሚዎችም በዚሁ መንፈስ ሀገርን ማገልገል ይገባናል ሲሉ በአጽኖት ተናግረዋል።

Share this post