የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሐረሪ ክልል ለሚገኙ የሐረር ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በጎ-ፍቃደኛ ተማሪዎች ሥልጠና ሰጠ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በተያዘው በጀት ዓመት ካከናወናቸው በርካታ ተግባራት መካከል በተለያዩ ክልሎችና ከተማ መስተዳድሮች ውስጥ ለሚገኙ የብሔራዊ ዩኒቨርስቲ በጎ-ፍቃደኛ ተማሪዎች ስለምርጫ ሂደትና ስለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ በቂ ግንዛቤ እንዲያገኙ የሚያስችል ትምህርቶችንና መረጃዎችን ተደራሽ ማድረግ ይጠቀሳል። በተያዘው ወር ሥልጠናው ከተሰጣቸው በጎ-ፍቃደኛ ወጣቶች ውስጥ 25 የሐረሪ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ተማሪዎች ሲኖሩበት፤ ቦርዱ ቀደም ሲል ከሰባት ዩኒቨርስቲዎች ለተውጣጡ በጎ-ፍቃደኛ ተማሪዎች፤ በያሉበት ክልሎችና ከተማ መስተዳድሮች ሆነው ሥልጠናውን እንዲወስዱ አድርጓል።
የቦርዱ የሥነ-ዜጋ እና የመራጮች ትምህርት ሥራ ክፍል ከቦርዱ የሐረሪ ክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ጋር በመተባበር በሰጠው በዚኽ ሥልጠና ላይ፤ የሥነ-ዜጋና የመራጮች ትምህርት ምንነት፣ የትምህርቱ ይዘት፣ ትምህርቱ የሚያስፈልጋቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች የትኞቹ ናቸው የሚለው፣ እንዲሁም ትምህርቱ አካታችነትን መርኅ ባደረገ መልኩ ለሁሉም የማኅበረሰብ ክፍሎች ተደራሽ የሚሆንባቸው ሥነ-ዘዴዎችን የተመለከቱ አጀንዳዎች ተካተውበታል።











