Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለጋምቤላ እና ለጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ በጎ፟-ፍቃደኛ ተማሪዎች ሥልጠና ሰጠ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም የሥነ ዜጋ እና የመራጮች ትምህርት በመስጠት ላይ መሆኑ ይታወቃል። ከነዚኽም አማራጮች አንዱ በተለያዩ ክልሎችና ከተማ መስተዳድሮች በሚገኙ ብሔራዊ ዩኒቨርስቲዎች ለሚማሩ በጎ-ፍቃደኛ ተማሪዎች ትምህርቱን በመስጠት በተዋረድ ለአካባቢያቸው ማኅበረሰብ ግንዛቤ እንዲፈጥሩ ማስቻል ይጠቀሳል። ቦርዱ በያዝነው ወር ለጋምቤላ እና ለጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ በጎ-ፍቃደኛ ተማሪዎች ሥልጠናውን የሰጠ ሲሆን፤ ቀደም ሲልም በአምስት የተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች ለሚገኙ በጎ-ፍቃደኛ ተማሪዎች ሥልጠናውን ሰጥቷል።

የቦርዱ የሥነ ዜጋ እና የመራጮች ትምህርት ሥራ ክፍል ከቦርዱ የጋምቤላ እና የሶማሌ ክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ጋር በመተባበር ከጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ለተውጣጡ 25 እንዲሁም ከጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ለተውጣጡ 25 ተማሪዎች፤ በድምሩ ከሁለቱ ዩኒቨርስቲዎች ለተውጣጡ 50 በጎ-ፍቃደኛ ተማሪዎች ሁለት ቀን የወሰደ ሥልጠና በያሉበት ክልል ሰጥቷል። የሥነ-ዜጋና የመራጮች ትምህርት ምንነት፣ የትምህርቱ ይዘት፣ ትምህርቱ የሚያስፈልጋቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች የትኞቹ ናቸው የሚለው፣ እንዲሁም ትምህርቱ አካታችነትን መርኅ ባደረገ መልኩ ለሁሉም የማኅበረሰብ ክፍሎች ተደራሽ የሚሆንባቸው ሥነ-ዘዴዎች ሥልጠናው ትኩረት ካደረገባቸው አጀንዳዎች ውስጥ ይጠቀሳሉ።

Share this post