ቦርዱ “የሥነ-ዜጋና የመራጮች ትምህርት እና ሁሉን አካታች የምርጫ ተሣትፎ” የተሰኘ የማኅበረሰብ ቲያትር በአዳማ ከተማ አካሄደ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ “የሥነ-ዜጋና የመራጮች ትምህርት እና ሁሉን አካታች የምርጫ ተሣትፎ” በሚል ርዕስ የማኅበረሰብ ቲያትር በአዳማ ከተማ በናፍያድ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት አካሄደ። ምርጫ ሁሉንም የማኅበረሰብ ክፍሎች የሚያካትት መሆኑንና አካል ጉዳተኛ ዜጎች ዲሞክራሲያዊ መብታቸው የሚያስገኝላቸውን የመምረጥ መመረጥ መብታቸውን ተግባራዊ ከማድረግ ወደ’ኋላ ሊያስቀራቸው እንደማይገባ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ታስቦ በተዘጋጀው የማኅበረሰብ ቲያትር ላይ የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች፣ መምህራን እንዲሁም የአስተዳደር ሠራተኞች የተሣተፉበት ሲሆን፤ ቲያትሩም በአማርኛና በአፋን ኦሮሞ ቋንቋዎች ቀርቧል። በቲያትሩ ላይ መስማት የተሳናቸው ተሣታፊዎችን ከግምት ውስጥ በማስገባት በምልክት ቋንቋ እንዲከታተሉት ተደርጓል።
ቦርዱ ኔት-ወርክ ኦፍ አክሽን ፎር ቪዥዋሊ ኢምፔርድ ኤንድ ዘ¬¬-ብላይንድ ከተባለ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የማኅበረሰብ ቲያትር ሙሉ ክፍል የተቀረጸ ሲሆን፤ በቀጣይም በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን አማራጮች ለሕዝብ ተደራሽ እንዲሆን የሚደረግ ይሆናል።










