Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለባሕር ዳር እና ለአሶሳ ዩኒቨርሲቲ በጎ-ፈቃደኛ ተማሪዎች በሥነ-ዜጋና በመራጮች ትምህርት ላይ ያተኮረ ሥልጠና ሰጠ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዜጎች የሥነ¬-ዜጋና የመራጮች ትምህርት ላይ የተሻለ መረዳት እንዲኖራቸው ለማስቻል በማሰብ በተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች ለሚገኙ በጎ-ፈቃደኛ ተማሪዎች ሥልጠና መስጠት መጀመሩ ይታወቃል። ቀደም ሲል ቦርዱ ለአዲስ አበባ፣ ለሰመራ እንዲሁም ለድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በጎ-ፈቃደኛ ተማሪዎች ሥልጠናውን የሰጠ ሲሆን፤ አሁን ደግሞ ለባሕር ዳር እና ለአሶሳ ዩኒቨርሲቲ በጎ-ፈቃደኛ ተማሪዎች ሥልጠናውን ሰጥቷል።

የቦርዱ የሥነ-ዜጋና የመራጮች ትምህርት ሥራ ክፍል ከቦርዱ የክልልና የከተማ መስተዳድር ቅ/ጽ/ቤቶች ጋር በመተባበር የሚሰጠውን ሥልጠና፤ ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ለተወጣጡ 26 በጎ-ፍቃደኛ ወጣቶች፤ በተመሳሳይም መልኩ ከአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ለተወጣጡ 25 በጎ-ፈቃደኛ ተማሪዎች በያሉበት ክልል ሰጥቷል። የሥነ-ዜጋና የመራጮች ትምህርት ምንነት፣ የትምህርቱ ይዘት፣ ትምህርቱ የሚያስፈልጋቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች የትኞቹ ናቸው የሚለው፣ እንዲሁም ትምህርቱ አካታችነትን መርኅ ባደረገ መልኩ ለሁሉም የማኅበረሰብ ክፍሎች ተደራሽ የሚሆንባቸው ሥነ-ዘዴዎች ሥልጠናው ትኩረት ካደረገባቸው አጀንዳዎች ውስጥ ይጠቀሳሉ።

በቀጣይም ቦርዱ ትምህርቱ ተደራሽ ባልሆነባቸው ብሔራዊ ዩኒቨርስቲዎች ላሉ በጎ-ፍቃደኛ ተማሪዎች ሥልጠናውን በመስጠት፤ ተማሪዎቹ ለአካባቢያቸው ማኅበረሰብ በተዋረድ ያገኙትን ዕውቀት እንዲያጋሩ በማድረግ፤ ዜጎች በዕውቀት ላይ የተመሠረተ የምርጫ ሥርዓት ተሣታፊ እንዲሆኑ የማስቻል ሥራውን የሚሠራ ይሆናል።

Share this post