Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሴት እና አካል ጉዳተኛ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትና አመራሮች ፖለቲካዊ ተሣትፏቸና የሚደርሱባቸው ተግዳሮቶችን የተመለከተ ሥልጠና ሰጠ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሴት እና አካል ጉዳተኛ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትና አመራሮች ፖለቲካዊ ተሣትፏቸውና የሚደርሱባቸው ተግዳሮቶችን የተመለከተ ሥልጠና ከሰኔ 1 እስከ ሰኔ 4 ቀን 2017 ዓ.ም. ሰጠ። ሴት እና አካል ጉዳተኛ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትና አመራሮች ወደ ፖለቲካ ተሣትፎ ሲመጡና በአመራርነት ሲሠሩ፤ እንዲሁም በምርጫ ወቅት ጭምር የሚያጋጥሟቸውን ተግዳሮቶችና መወሰድ ስላለባቸው የመፍትሔ ዕርምጃዎችን የተመለከተ ግንዛቤ መፍጠር ዐላማው አድርጎ የተሰጠውን ሥልጠና በንግግር የከፈቱት የቦርዱ ሰብሳቢ ወ/ሮ ሜላትወርቅ ኃይሉ ሲሆኑ፤ በንግግርቸውም ቦርዱ እንደ አዲስ ሲቋቋምና ዐዋጅ ሲረቅ በዋነኝነት ታሳቢ ካደረጋቸው ነገሮች ውስጥ ሕጉ የሴቶችና የአካል ጎዳተኞች ተሣትፎን የሚያበረታቱ ድንጋጌዎች እንዲካተቱበት ማድረጉን በዋነኝነት ጠቅሰው፤ ቦርዱ በዛ ሳይወሠን በጉዳዩ ላይ የተለያዩ ሥልጠናዎችን ሲሰጥ የቆየ ቢሆንም አሁንም ብዙ መሥራት እንደሚጠይቅ ተናግረዋል። ቦርዱ ባሻሻለውና እንዲፀድቅለት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በላከው ዐዋጅ ላይ የሴቶችና የአካል ጉዳተኞች ተሣትፎን የበለጠ ለማበረታታት የሚያስችል የሕግ ድንጋጌዎችን እንዲካተቱ ማድረጉን የገለጹት ሰብሳቢዋ፤ በጉዳዩ ላይ የተሻለ መፍትሔ ማምጣት ከተፈለገ በስትራቴጂ የተደገፉ ሥራዎችን መሥራት እንደሚጠይቅም አብራርተዋል።

ቦርዱ የሴቶችና የአካል ጉዳተኞችን ተሣትፎን ለማበረታታት በማሰብ የሚያደርገውን ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ ተከትሎ፤ እንደ ቅድመ ሁኔታ ፓርቲዎች የሚያቀርቧቸው የፓርቲው ሴቶች እና አካል ጉዳተኛ አባላት ቁጥር እንዲሁም አመራሮች ብዛት ላይ የተሳሳተ መረጃ በሚያቀርቡበት ጊዜ ገንዘቡ ተመላሽ እንዲሆን የሚያደርገውና በሕጉ አስገዳጅነት እስከ ማገድና መሠረዝ የሚደርስ ውሣኔዎችን የሚያሳልፍበት ዋነኛ ምክንያት ገንዘብ የማስመለስ ጉዳይ ሣይሆን፤ ፓርቲዎች ሴቶችን እና አካል ጉዳተኞችን በአባልነት እና በአመራር ለማምጣት የሚደረገውን ጥረት ትኩረት እንዲሰጡት ለማድረግ ታስቦ እንደሆነ አጽንዖት ሰጥተው ተናግረዋል።

በጉዳዮ ላይ ሳይንሳዊ መንገድ ተከትሎ የተሠሩ ጥናቶችን መሠረት አድርጎ ሁሉም በግል የሚያደርገውን ጥረት በጋራ በማምጣት፤ መማማርና ልምድ መለዋወጥ እንዲቻ፤ በዘርፉ ላይ ጥናት ያደረጉት ባለሞያ ለዶ/ር ፍሬሕይወት ስንታየሁ እና የቦርዱ ሥርዓተ ፆታ ዕኩልነትና ማኅበራዊ አካታችነት ሥራ ክፍል ኃላፊዋ ክብረወርቅ ንጉሤ እንዲሁም ከፍተኛ የሥርዓተ ፆታ ባለሞያዋ ዮርዳኖስ ተወልደ በሰጡት ሥልጠና ላይ፤ ሴቶችና አካል ጉዳተኞች ወደ ፖለቲካ ፓርቲ ተሣትፎና ወደ አመራርነት እንዳይመጡ የሚያደርጓቸው ተግዳሮቶች ምንድናቸው የሚለውን የመለየት ሥራና ምን መፍትሔ መወሰድ ይገባል በሚለው ላይ ተሣታፊዎቹ ግንዛቤ እንዲያገኙ የተደረገ ሲሆን፤ ይኽም ሲሆን ከራሳቸው ከሴቶቹና ከአካል ጉዳተኞቹ፣ ከፓርቲዎች፣ ከሲቪል ማኅበረሰብ ተቋማት፣ ከመንግሥት እና ከምርጫ ቦርድ ምን ይጠበቃል የሚለውም በስፋት ለውይይት ቀርቧል።

አሣታፊ በነበረው ሥልጠና ላይ ፆታና ሥርጻተ-ፆታ እንዲሁም በፓርቲ ውስጥና ባጠቃላይ በፖለቲካዊ ምኅዳሩ ውስጥ እንዲሁም በምርጫ ወቅት የሚያጋጥሙ ፆታን መሠረት አድርገው የሚፈጸሙ ጥቃቶች የትኞቹ ናቸው የሚለውን በመለየት፤ መፍትሔዎቻቸውስ ምንድን ናቸው የሚለውም እንዲሁ በዝርዝር ታይቷል። ተሣታፊዎች በጠቀሱት ርዕሰ-ጉዳዮች ላይ በቡድን እንዲወያዩበት የተደረገ ሲሆን፤ ሁሉም የውይይታቸው ግኝቶችን በቡድን ተወካዮቻቸው አማካኝነት እንዲያቀርቡት ተደርጓል።

የቦርዱ ሰብሳቢ በሥልጠናው መጨረሻም ባደረጉት ንግግርም፤ ቦርዱ ከሥልጠናው ቀደም ብሎ ሴቶች እና አካል ጉዳተኛ ፖለቲከኞች ያሉባቸውን ተግዳሮቶች አስመልክቶ ያስጠናው ጥናት ውጤት ለሥልጠናው መዘጋጀት እንደምክንያት ጠቅሰው፤ ውጤት መምጣት የሚችለው ተሣታፊዎቹ ከሥልጠናው ያገኙትን ዕውቀት በተዋረድ ለአባላቶቻቸውና በዙሪያቸው ላሉ የማኅበረሰብ ክፍሎች ማስተማር ሲችሉ መሆኑን አሳስበዋል።

ቦርዱን ጨምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ትኩረት ሰጥተው መሥራት እንደሚጠበቅባቸው የገለጹት ሰብሳቢዋ፤ የዚኽ ሁሉ ጥረት ውጤት በ7ኛው ዙር ሀገራዊ ምርጫ ላይ እንደሚታይ ያላቸውን ዕምነት ገልጸዋል። በመጨረሻም ሥልጠናውን ለሰጡ ባለሞያዎችና ተሣታፊዎች እንዲሁም ላስተባበረው የቦርዱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉዳይ ሥራ ክፍል ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

Share this post