የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በቴክኖሎጂ የታገዘ የምርጫ አስተዳደር ሥርዓት መተግበሪያውን ለባለድርሻ አካላት አስተዋወቀ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በቴክኖሎጂ የታገዘ የምርጫ አስተዳደር ሥርዓት መተግበሪያውን ለፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና ተወካዮች እንዲሁም ለሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አስተዋወቀ። ከሰኔ 2 እስከ ሰኔ 3 ቀን 2017 ዓ.ም. የተካሄደውን የማስተዋወቂያ መርኅ-ግብር በንግግር የከፈቱት የቦርዱ ሰብሳቢ ወ/ሮ ሜላትወርቅ ኃይሉ ሲሆኑ፤ በንግግራቸውም ቦርዱ የስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫን ማስፈጸሙ ተከትሎ የምርጫ ሥርዓቱን ለማዘመን ያግዛሉ ያላቸውን በርካታ ሥራዎች ሲሠራ መቆየቱን አስታውሰው፤ ከነዚኽም ውስጥ በባለድርሻ አካላት በተለያዩ ጊዜ አስተያየት ሲሰጥበት የነበረው ዘመናዊ የምርጫ አስተዳደር ሥርዓትን ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በመሥራት መራጮችና ዕጩዎች በቴክኖሎጂ ታግዘው የሚመዘገቡበትን መተግበሪያ ማበልጸጉን ተናግረዋል።
ይኽ ትግበራ የቴክኖሎጂ ኢንፍራስትራክቸር በተዘረጋባቸው አካባቢዎች በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ ታስቦ የተዘጋጀው መተግበሪያ ሲሠራ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንደተደረገ የተናገሩት ሰብሳቢዋ፤ ለደኅንነት ሥጋት ሊኖረው የሚችለውን ተጋላጭነት ለማስቀረት ሲስተሙን ከውጭ ከመግዛት ይልቅ በራስ ዐቅም በባለሞያዎች በማበልጸግ የቴክኖሎጂ ሥርዓቱ ዋነኛ ባለቤትና ተቆጣጣሪ ምርጫ ቦርዱ እንዲሆን በሚያስችል አግባብ እንደተዘጋጀ አብራርተዋል።
በቴክኖሎጂ ስለሚታገዘው ሥርዓት ጠቀሜታ ሲያብራሩም፤ ምርጫ በመጣ ቁጥር መራጮችን እንደ’አዲስ የተለያየ ቁጥር በመስጠት የሚከናወን የአመዘጋገብ ልማድን በማስቀረት ቋሚ የመራጮች መታወቂያ ቁጥርና መዝገብ በማኖር፤ መራጮች እንደ አዲስ መታወቂያ ማውጣት ሳይጠበቅባቸው ቋሚ ቁጥራቸውን በማስገባት ብቻ የሚመዘገቡበት ሥርዓት በማበጀት፤ መራጮችን ለመመዝገብ የሚጠፋውን ገንዘብ፣ ጊዜና ጉልበት እንዲሁም ጥቅም ላይ የሚውሉ የምርጫ ቁሳቁስ ወጪዎችን መቀነስ እንደሚያስችል አብራርተዋል።
መተግበሪያው ከላይ ከተጠቀሱት ጠቀሜታዎች ባለፈ በአንድ ምርጫ ሁለቴና ከዛ በላይ ለመመዝገብና ለመምረጥ የሚደረግን ሕገ-ወጥ ተግባር በማስቀረት ዕጩዎች ፍትሐዊ በሆነ መልኩ ድምፅ እንዲያገኙ የሚያስችል ሲሆን፤ አኃዛዊ የሆኑትን ጨምሮ መረጃዎችን በቀላሉ ለማደራጀትም እንዲሁ ያግዛል።
በእጅ ስልክ አማካኝነት በራስ፤ እንዲሁም በቦርዱ ባለሞያዎች አጋዥነት በቴክኖሎጂ በመታገዝ የሚደረግ የመራጮች ምዝገባ ሥርዓት፣ በሌላ በኩል የግልና የፖለቲካ ፓርቲ ዕጩዎች ባሉበት ቦታ ወይም በጽ/ቤታቸው በመሆን በቴክኖሎጂ በመታገዝ የሚያከናውኑት የዕጩነት ምዝገባ ሥርዓት፤ እንዲሁም በድምፅ መስጫ ቀን መራጮች በምርጫ ጣቢያ በአካል በመገኘት በቴክኖሎጂ የታገዘ የመራጭነት ማመሳከሪያ በማድረግ የሚከናወን ድምፅ የመስጠት ሂደት ምን ሊመስል እንደሚችል በቅድም ተከተል ተሣታፊዎች እንዲያዩት የተደረገ ሲሆን፤ ይኽንንም ተከትሎ ተሣታፊዎቹ ባዩት ነገር እንደረኩና ለቦርዱም ትልቅ አድናቆት እንዳላቸው ገልጸው፤ በቴክኖሎጂ የታገዘው የመራጮችና የዕጩዎች የምዝገባ ሥርዓት ተግባራዊ በሚደረግበት ወቅት ሊከሰቱ የሚችሉ ተገማችና ተገማች ላልሆኑ ዕክሎች ቦርዱ ምን መፍትሔ አዘጋጅቷል ሲሉ በርካታ ጥያቄዎችን አንስተዋል። ለቀረቡት ጥያቄዎች የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ መልስ የሰጡ ሲሆን፤ ቴክኒካል ለሆኑት ሞያዊ ጥያቄዎች ደግሞ በቦርዱ ባለሞያ አማካኝነት መልስ ተሰጥቶባቸዋል።
ለጊዜው በከፊል ተግባራዊ ይደረጋል ተብሎ የታሰበው መተግበሪያን የደኅንነት ሥጋት አስመልክቶ ለቀረበው ጥያቄ የቦርዱ ባለሞያው መልስ ሲሰጡም፤ መተግበሪያው በርካታ የደኅንነት መፈተሻ ሥርዓቶችን ያለፈ እንደሆነና ጥብቅ ቁጥጥር እንደሚደረግበት ተናግረዋል።
መተግበሪያው ተግባራዊ በሚደረግባቸው አካባቢዎች ጎን ለጎን የቦርዱ ባለሞያዎች የማስተባበር ሥራ እንደሚሠሩና፤ ተግባራዊ በማይደረግባቸው አካባቢዎች ግን ቀደም ሲል በነበረው የማንዋል ሥርዓት ምርጫው እንደሚደረግ ዋና ሰብሳቢዋ ገልጸዋል። ቦርዱ መተግበሪያውን በሚያበለጽግበት ጊዜ ከፍተኛ ትኩረት ካደረገባቸው ጉዳዮች ውስጥ የደኅንነት ጉዳይና አካታችነት ዋነኞቹ እንደሆኑና፤ በቀጣይ መተግበሪያው በዐዋጅ ፀድቆ ለሕዝብ ይፋ በሚያደርግበት ጊዜም በማስተዋወቅያ መድረኩ ላይ የተሰጡ ግብዓቶችንና ዐዋጁ ላይ የተቀመጡትን ድንጋጌዎች ከግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ የበለጠ ዳብሮ እንደሚሆን ሰብሳቢዋ በአጽንዖት ተናግረዋል።