Skip to main content

ቦርዱ “የማኅበረሰብ ቲያትር ለአካታች የሥነ-ዜጋና የመራጮች ትምህርት" የተሰኘው መርኅ-ግብር በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወላይታ ዞን አካሄደ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ “የማኅበረሰብ ቲያትር ለአካታች የሥነ-ዜጋና የመራጮች ትምህርት” የተሰኘ መርኅ ግብር በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በወላይታ ዞን አካሄደ። በተጠናቀቀው ግንቦት ወር 2017 ዓ.ም. ለተከታታይ ዘጠኝ ቀናት የተካሄደው መርሐ-ግብር ማስጀመሪያ በወላይታ ሶዶ ከተማ ሁለተኛ ደረጃ መሰናዶ ትምህርት ቤት የተካሄደ ሲሆን፤ በትምህርት ቤት ውስጥ ያሉትን ከ74 በላይ አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ከግምት ውስጥ በማስገባትም በሥነ-ሥርዓቱ ላይ አካታችነትን የሚያስተምረውን ቲያትር መስማት ለተሳናቸው ታዳሚያን በቀጥታ ተተርጉሞ ቀርቧል።

ቦርዱ ውመን ኢን ማይስ ኢትዮጵያ ከተባለ የሲቪል ማኅብረሰብ ድርጅት ጋር በመተባበር ባዘጋጀው ቲያትር ላይ አካል ጉዳተኝነት አለመቻል እንዳልሆነና የምርጫ ሂደት ሁሉንም የማኅበረሰብ ክፍሎች የሚያካትት እንደሆነ መልዕክት የተላለፈ ሲሆን፤ የመርኅ-ግብሩ ሙሉ ክፍል በምልክት ቋንቋ እየተተረጎመ መስማት ለተሳናቸው ተማሪዎች ተደራሽ እንዲሆን ከመደረጉም ባለፈ የተለያዩ በራሪ ወረቀቶች ለታዳሚ ተማሪዎች እና ዝግጅቱን ለተሣተፉ እንግዶች ተደራሽ ተደርጓል።

በተመሳሳይ መልኩ በአረካ ከተማ አስተዳደር (በአረካ ማክሰኞ ገበያ እና በአረካ ከተማ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት) እንዲሁም በኪንዶ ኮይሻ በሌ ሐዋሳ ከተማ አስተዳደር (ሐሙስ ገበያ ላይ) ተመሳሳይ መልዕክት በማስተላለፍ ግንዛቤ ማስጨበጥ ተችሏል። ሁሉም መርኅ-ግብሮች በወላይታ ቴሌቪዥን እና በወጌታ ኤፍ.ኤም ሬድዮ ዜና አገልግሎት ተደራሽ የተደረጉ ሲሆን፤ በተጨማሪም ብዙ ተከታይ ባላቸው የማኅበራዊ ሚዲያዎች ለተቀረው የአካባቢበው ማኅበረሰብ ተደራሽ ለማድረግ ተችሏል።

Share this post