ቦርዱ የ6ኛው ሀገራዊ ምርጫን ተከትሎ በወሰዳቸው ሦስት ቁልፍ የምርጫ ሥርዓት ማዘመኛ ማሻሻያዎችን በተመለከተ ዎርክሾፕ አካሄደ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫን መፈጸም ተከትሎ ሁሉምን ባለድርሻ አካላት፤ መገናኛ ብዙኃኑን ጨምሮ በተናጠል የስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫን ስኬትና ተግዳሮት ተብለው ሊጠቀሱ የሚችሉትን ጉዳዮች በዝርዝርና በጥልቀት በመወያየት፤ የውይይቱንም ግኝት (Lesson Learned) ሁሉንም ባለድርሻ አካላት በአንድ ላይ ባሣተፈ መልኩ በድጋሚ አስተችቶ የማሻሻያ መፍትሔዎችን መውሰድን የቅድሚያ ቅድሚያ ተግባሩ አድርጎ ሲሠራ ቆይቷል።
ቦርዱ በባለድርሻ አካላት ማሻሻያ ተጠይቆባቸው የመፍትሔ ዕርምጃ ከወሰደባቸው ዋና ዋና አጀንዳዎች ውስጥ ለአፈጻጸም አስቸጋሪ የነበሩትን የዐዋጁ አንቀጾችን በመለየት ሀገራዊ ተጨባጭ ሁኔታዎችን እና ዓለም ዐቀፍ ተሞክሮዎችን ባገናዘበ መልኩ የማሻሻያ ሃሳቦችን በባለሞያ አስጠንቶ ማቅረብ፣ የዕጩዎችንና የመራጮችን መጉላላት የሚያስቀር እና መረጃንም ዘመናዊ ሥርዓትን ጠብቆ ለማደራጀት የሚያግዝ የዲጂታይዜሽን ሥራ መሥራት ይጠቀሳሉ።
በተጨማሪም ቦርዱ በቃልና በተግባር ሲወራረስ የመጣውን ወጥነት የጎደለው የምርጫ አተገባበር ሥርዓትና ዕውቀትን እንዲሁም የባለሞያዎች መተካካት በሚኖርበት ወቅት ሊከሰት የሚችለውን ሞያዊ ክፍተትን ለማስቀረት እንዲረዳ፤ ከዛም ባለፈ የቦርዱ ሥራ ክፍሎች በተናጠል እና በጋራ የሚኖራቸውን ዝርዝር ኃላፊነቶችና ለይቶ በማውጣት የሚና መደበላለቅ ሳይፈጠር የበለጠ ተናቦ መሥራት እንዲቻልና በውጤቱም ወጥነት ያለው የምርጫ ተግባራትን ለማከናወን የሚያግዝ ማጣቀሻ “የምርጫ ተግባራት ማንዋል” በራሱ ባለሞያዎች አሠርቶ ለግምገማ አቅርቧል።
ቦርዱ በተያዘው ሣምንት መጀመሪያ ላይ ከላይ የተጠቀሱትን በቴክኖሎጂ የታገዘ የምርጫ ሥርዓት፣ የዐዋጅ ማሻሻያ እና የምርጫ ተግባራት ማንዋልን የተመለከተ የሦስት ቀናት ዎርክ-ሾፕ አካሂዷል። አምስቱም የቦርድ አመራሮች፣ የጽ/ቤት ኃላፊዎች፣ የዋናው መሥሪያ ቤት የሥራ ክፍል ኃላፊዎችና ከፍተኛ ባለሙያዎች እንዲሁም የቦርዱ የክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊዎች የተገኙበትን ዎርክ-ሾፕ በንግግር የከፈቱት የቦርዱ ሰብሳቢ ወ/ሮ ሜላትወርቅ ኃይሉ ሲሆኑ፤ በንግግራቸውም ይኽ ዎርክ-ሾፕ ሁሉም የቦርዱ ኃላፊዎችና ባለሞያዎች በተለዩ የዐዋጁ አንቀጾች ላይ የተደረጉ ማሻሻያዎችን፣ በቴክኖሎጂ የታገዘ የምርጫ ማስፈጸሚያ ሥርዓት አተገባበርን፣ እንዲሁም በራስ ዐቅም የተዘጋጀውን የምርጫ ማስፈጸሚያ ማንዋል ዝርዝር በተመለከተ የጋራ መረዳት እንዲኖር ከማስቻል ባሻገር፤ በቦርዱ ውስጥ ያለውን በትብብር የመሥራት መንፈስ የበለጠ እንደሚያጎለብትም ጭምር ያላቸውን ዕምነት ገልጸዋል።
ሦስት ቀናትን በወሰደው ዎርክ-ሾፕ ላይ የመራጮች እና የዕጩዎች ምዝገባን በቴክኖሎጂ ታግዞ እንዴት ባለ ቅደም-ተከተል መፈጸም እንደሚቻል በባለሞያዎች ገለጻ ተሰጥቶ ተሣታፊዎቹ ሲስተሙን በተግባር እንዲፈትሹት ተደርጓል። የዐዋጁን ማሻሻያ በተመለከተም እንዲሁ በቦርዱ የሕግ ሥራ ክፍል ኃላፊና በባለሞያዎች አማካኝነት ማብራሪያ የተሰጠ ሲሆን፤ በመጨረሻም በቦርዱ ባለሞያዎች ተዘጋጅቶ የቀረበው የቅድመ-ምርጫን፣ የምርጫን እንዲሁም የድኅረ-ምርጫን ተግባራት በዝርዝር የሚያስረዳው “የምርጫ ተግባራት ማንዋል” ለተሣታፊዎቹ በአዘጋጅ ባለሞያዎቹ አማካኝነት ቀርቦ የማጠናከሪያ ሃሳብ በተሣታፊዎቹ ተሰጥቶበታል።
በዎርክ-ሾፑ መጠናቀቂያ ላይ የመዝጊያ ንግግር ያደረጉት የቦርዱ ሰብሳቢ፤ ሞያዊ ማብራሪያዎችን ሲያቀርቡ ለነበሩት ባለሞያዎችና ገንቢ አስተያየቶችን ሲሰጡ ለነበሩት ተሣታፊዎች ያላቸውን አድናቆት የገለጹ ሲሆን፤ ለተሠራው ሥራ ትልቅ አክብሮት እንዳላቸው ተናግረዋል። ምርጫውን ተዓማኒነቱንና አካታችነቱን ጠብቆ ወደ ዘመናዊ የአሠራር ሥርዓት እንዲሸጋገር ማድረጉ 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ላይ የተሻለ አፈጻጸም እንዲኖር እንደሚያስችል ያላቸውን ዕምነት ገልጸዋል። የተዘጋጀው የምርጫ መተግበሪያ ማንዋልን በተመለከተ ባደረጉት ንግግርም ዕውቀት በግለሰቦች ተወሥኖ እንዳይቀርና ወጥ የአሠራር ሥርዓትን ለመዘርጋት እንደሚያስችል፤ ይህም ቀጣይነት ያለው ተቋሟዊ መማማርን ባህል ለማድረግ በር ከፋች እንደሚሆን በአፅንዖት ገልጸዋል።
