Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በሥነ-ዜጋና የመራጮች ትምህርት ርዕሰ-ጉዳይ ላይ የሰጠው የአሠልጣኞች ሥልጠናን የተመለከተ የልምድ ልውውጥ አካሄደ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሀገሪቱ ውስጥ ባሉ የተለያዩ ብሔራዊ ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ ላሉ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በሥነ-ዜጋና የመራጮች ትምህርት ርዕሰ-ጉዳይ ላይ ሥልጠና በመስጠት ላይ መሆኑ ይታወቃል። ይኽንንም ተከትሎ ቦርዱ ቀደም ሲል ሥልጠናውን በተሰጠባቸው በሲዳማ እና በአፋር ክልሎች እንዲሁም በአዲስ አበባ እና በድሬደዋ ከተማ መስተዳድሮች “በሙከራ ትግበራ ማዕቀፍ” ከአራት ዩኒቨርሲቲዎች ለተውጣጡ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በሥነ-ዜጋና በመራጮች ትምህርት ርዕሰ-ጉዳይ ላይ የሰጠው የአሠልጣኞች ሥልጠና ያስገኘው ውጤትና ያጋጠሙ ተግዳሮቶች፤ እንዲሁም የትኞቹ የሥልጠና ሥልቶች ውጤት አስገኙ የሚለው ላይ የልምድ ልውውጥ አካሄደ።

በቦርዱ ዋና መሥሪያ ቤት የሚገኙ የሥራ ክፍል ኃላፊዎችና የክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊዎች የተሣተፉበትን የልምድ ልውውጥ መድረክ በንግግር የከፈቱት የቦርድ አመራር አባሉ ዶ/ር አበራ ደገፋ ሲሆኑ፤ በንግግራቸውም እንደ ቦርድ የጀመርነው ሥራ አበረታች ቢሆንም፤ የሥነ-ዜጋና የመራጮች ትምህርትን በሚፈለገው ጥራትና ደረጃ ተደራሽ ለማድረግ ከምናደርገው ሁለንተናዊ ጥረት ባሻገር ትምህርቱን በተጨባጭ በታችኛው የአስተዳዳር መወቅር ለሚኖሩ ዜጎች እንዲዳረስ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፤ በተለይም የመራጮች ትምህርትን ለመስጠት ሕጋዊ ዕውቅና ያላቸው ድርጅቶች ሚና የላቀ መሆኑን ተናግረዋል። ቦርዱ ያሠለጠናቸው ተማሪዎች ወደ ማሠልጠን ተግባር ገብተው ማኅበረሰባቸውን በሥነ-ዜጋ እና በመራጮች ትምህርት በቂ ግንዛቤ እንዲያገኙ በማድረግ፤ በዕውቀት ላይ ተመሥርተው የሚያስተዳደራቸውን ወኪል የሚመርጡ ዜጎች መፍጠር እንደሚገባ የገለጹት አመራሩ፤ ይኽንንም ለማረጋገጥ አስቻይ የአሠራር ሥርዓት መዘርጋት ይገባል ብለዋል፡፡

በተጠቀሱት ሁለት ክልሎች እና ሁለት ከተማ መስተዳድሮች እያንዳንዳቸው 25 በድምሩ 100 በጎ ፈቃደኛ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች “የሥነ-ዜጋና የመራጮች ትምህርት ምንነትና መርኆች፣ ሥርዓተ መንግሥት እና የመንግሥት አወቃቀር፣ በኢትዮጵያ የሚካሄዱ የምርጫ ዓይነቶች፣ የድምፅ አሰጣጥ ሂደት እና መሰል ጉዳዮች”ን በተመለከቱ ርዕስ-ጉዳዮች ላይ ሥልጠና የወሰዱ ሲሆን፤ በሥልጠናው ያካበቱትን ዕውቀትም ለሚኖሩበት የኅብረተሰብ ክፍል በአግባቡ እንዲያጋሩና በዘርፉ የሚፈለገው ግንዛቤ እንዲጎለብት በሚያስችል መልኩ ዝግጁ መደረጋቸው ተገልጿል።

በሥልጠናው ላይ ተሣታፊ የነበሩ ሥልጠናው ተግባራዊ ባልተደረገባቸው ክልሎች የሚገኙ የቦርዱ ቅ/ጽ/ቤት ኃላፊዎች፤ በልምድ ልውውጥ ወቅት ከተነሡት መልካም ተሞክሮዎች ጥሩ ልምድ እንደሚወስዱና ያጋጠሙ ውሥንነቶችንም በሚያስቀር መልኩ ሥልጠናውን በየክልላቸው ተግባራዊ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።

በልምድ ልውውጥ መድረኩ በከተሞች አካባቢ በብዛት የሚሰጠው የሥነ ዜጋና የመራጮች ትምህርት ወደ ዞኖችና ወረዳዎች ብሎም ወደ ቀበሌዎች በተዋደር ለዜጎች ተደራሽ እንዲሆን ዘርፈ ብዙ ሥራዎች ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመናበብ መሥራት እንደሚገባ በመድረኩ ተገልጿል፡፡

በሙከራ ትግበራ ሥልጠናው በሥነ-ዜጋና የመራጮች ትምህርት እንዲሰለጥኑ የአንደኛ፣ የሁለተኛ እና የሦስተኛ ዓመት የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ከሕግና፣ ከዓለም ዐቀፍ ግንኙነት እንዲሁም ከፖለቲካል ሳይንስ ትምህርት ክፍሎች በጎ-ፈቃደኛ ተማሪዎቹ የተመለመሉ ሲሆን፣ በምልመላውም ለሴቶችና ለአካል ጉዳተኞች አወንታዊ ድጋፍ መሰጠቱ ተነግሯል።

Share this post