Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለሰመራ ዩኒቨርሲቲ እና ለድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በጎ ፈቃደኛ ተማሪዎች ሥልጠና ሰጠ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በድኅረ ምርጫ ወቅት ከሚያከናውናቸው ዋና ዋና ተግባራት ውስጥ የሥነ¬-ዜጋና የመራጮች ትምህርት መስጠት መሆኑ ይጠቀሳል። በዐዋጁም ላይ ቦርዱ ይኽንን ተግባሩን በክልልና በከተማ መስተዳድር ደረጃ በሚቋቋሙ የቦርዱ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች አማካኝነት እንደሚያከናውን በተገለጸው መሠረት፤ የቦርዱ የሥነ-ዜጋና የመራጮች ትምህርት ሥራ ክፍል በተለያዩ ክልሎችና ከተማ መስተዳድሮች ከሚገኙ የቦርዱ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ጋር በመተባበር በየክልሉና ከተማ መስተዳድሮቹ ለሚገኙ የብሔራዊ ዩኒቨርስቲ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች፤ በሥነ-ዜጋና በመራጮች ትምህርት ዙሪያ ሥልጠና ሰጥቷል። በዚኽም አግባብ ቦርዱ ሥልጠናው ባልተሰጠባቸው ዩኒቨርስቲዎች ሥልጠናውን መስጠት ቀጥሎ፤ ለሰመራ ዩኒቨርሲቲ እና ለድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በጎ ፈቃደኛ ተማሪዎች ሰጥቷል።

ከሰመራ ዩኒቨርሲቲ ለተዉጣጡ 25 የበጎ ፍቃደኛ ወጣቶች፤ በተመሳሳይ ሁኔታ ከድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም በድሬዳዋ ከተማ ከሚገኙ ሁለት የፖሊ-ቴክኒክ ኮሌጆች ለተውጣጡ 25 በበጎ ፈቃደኝነት ሥራ ላይ ለመሠማራት ፍላጎት ላላቸው ተማሪዎች ባሉበት በተያዘው የግንቦት ወር ሥልጠናው የተሰጠ ሲሆን፤ ሥልጠናውም የሥነ-ዜጋና መራጮች ትምህርት ምንነት፣ የትምህርቱ ይዘት፣ ትምህርቱ የሚያስፈልጋቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች የትኞቹ ናቸው የሚለውን እንዲሁም ትምህርቱ አካታችነትን መርኅ ባደረገ መልኩ ለሁሉም ማኅበረሰብ ክፍሎች ተደራሽ የሚሆንባቸው ሥነ-ዘዴዎች ላይ ትኩረት አድርጎ ተሰጥቷል።

Share this post