Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫና ተያያዥ ጉዳዮችን የተመለከቱ የኅትመት ውጤቶችን በቤንሻንጉል-ጉሙዝ እና በአማራ ክልሎች አሠራጨ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዜጎች በሥነ-ዜጋና በመራጮች ትምህርት ዙሪያ ያላቸዉን ግንዛቤ ለማሳደግ ያግዛል ያላቸዉን ዘዴዎች በመጠቀም የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል። በዚህም መሠረት የቦርዱ የሥነ-ዜጋና መራጮች ትምህርት ሥራ ክፍል ከቦርዱ የክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ጋር በመቀናጀት በተለያዩ ቋንቋዎች የተዘጋጁ ምርጫና ተያያዥ ጉዳዮችን የተመለከቱ የኅትመት ውጤቶችን ለዜጎች ተደራሽ ለማድረግ ላይ በስፋት እየሠራ ይገኛል።

በመሆኑም የሥራ ክፍሉ በቦርዱ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በኩል በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ በሚገኙ በስድስት ወረዳዎች ማለትም በሆሞሻ፣ በአብርሀሞ፣ በመንጌ፣ በኡራ፣ በኩሙሩክ እና ባምባሲ ወረዳዎች እንዲሁም በአሶሳ ከተማ ሥር በሚገኙ በሁለት ኮሌጆች፣ በአንድ የሕዝብ ቤተ-መጻሕፍት፣ በዐሥራ ስድስት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ በ24 የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችና በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ የኅትመት ውጤቶችን ያሠራጨ ሲሆን፤ በተመሳሳይም በቦርዱ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በኩል በባህርዳር ከተማ ውስጥ ለሚገኙ በሰባት የሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤቶች፣ በአራት የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ በአንድ ኮሌጅ፣ በሁለት የሕዝብ ቤተ-መጽሐፍት እና በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ፤ ባጠቃላይ በሁለቱ ክልሎች በአማርኛ ቋንቋ እንዲሁም በብሬል የተዘጋጁ አምስት የተለያዩ ይዘት ያላቸው በቁጥር 9000 ብሮሸሮችና መጽሔቶችን እንዲሁም የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ሥነ-ምግባር ዐዋጅ ቁጥር 1162/2011 በቁጥር 350 በክልሎቹ ውስጥ ለሚገኙት የትምህርት ተቋማት አስረክቧል።

‘የምርጫ ሒደት’፣ ‘ምርጫ በኢትዮጵያ’፣ ‘ኢትዮጵያ ምን ዓይነት የምርጫ ሥርዓት ትከተላለች’፣ ‘ሰላማዊ ምርጫ በኢትዮጵያ’፣ እንዲሁም ‘ዴሞክራሲ እና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት’ የሚሉት በኅትመት ውጤቶቹ ከተካተቱት ርዕሰ ጉዳዮች ውስጥ ይጠቀሳሉ። ቦርዱ የሥነ- ዜጋና የመራጮች ትምህርትን ለዜጎች ተደራሽ ለማድረግ በአጋርነት አብሮ ከሚሠራቸዉ ባለድርሻ አካላት መካከል የትምህርት ተቋማት ከፍተኛውን ድርሻ የሚወስዱ በመሆናቸው ይህን መሰሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን ከባለድርሻ አካላት እና ከክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ጋር በመሆን ለወደፊትም አጠናክሮ የሚሠራ ይሆናል።

Share this post