የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በበጎ ፈቃደኝነት አገልግሎት ዙሪያ ሥልጠና ሰጠ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሥነ-ዜጋና የመራጮች ትምህርትን በሁሉም የሀገሪቱ ክልሎችና ከተማ መስተዳደሮች በአካታችነት ለማዳረስ እንዲቻል በየክልሎቹና ከተማ መስተዳድሮቹ ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች በጎ-ፍቃደኛ የሆኑ ወጣቶችን በመመልመል የሥነ-ዜጋና የመራጮች ትምህርትን በመስጠት ሂደት ውስጥ ተሣታፊ እንዲሆኑ ዕቅድ ይዞ ለተግባራዊነቱ በትኩረት እየሠራ ይገኛል።
በዚኽም መሠረት የቦርዱ የሥነ-ዜጋና የመራጮች ትምህርት ሥራ ክፍል ከቦርዱ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ጋር በመቀናጀት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተለያዩ የትምህርት ክፍሎች ለተውጣጡና ትምህርቱን ለመስጠት በፍቃደኝነት ለመሣተፍ ፍላጎት ላላቸው 25 የሁለተኛና ሦስተኛ ዓመት ተማሪዎች፤ በሥነ-ዜጋና መራጮች ትምህርት ይዘት እና አሰጣጥ ሥነ-ዘዴ ላይ ያተኮረ የሁለት ቀን ሥልጠና ሰጥቷል። ሥልጠናው ከግንቦት 9 እስከ ግንቦት 10 ቀን 2017 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢ ውስጥ በሥነ-ዜጋና መራጮች ትምህርት ባለሙያዎች የተሰጠ ሲሆን፤ በሥልጠናውም የሥነ-ዜጋና መራጮች ትምህርት ምንነት፣ የትምህርቱ ይዘት፣ ትምህርቱ የሚያስፈልጋቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች የትኞቹ ናቸው የሚለውን እንዲሁም ትምህርቱ አካታችነትን መርኅ ባደረገ መልኩ ለሁሉም ማኅበረሰብ ተደራሽ የሚሆንባቸው ሥነ-ዘዴዎች ላይ ሰፊ ገለጻ ተሰጥቶ፤ በማስከተልም በተማሪዎቹ መካከል የቡድን ውይይት ተደርጓል።
በሥልጠናው ማጠቃለያ ላይ በሥልጠናው ተሣታፊ የሆኑት ወጣቶች ወደ ማኅበረሰቡ ሲመለሱ ስለ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ምንነት እና የዜጎች ተሣትፎ ጠቀሜታን በተመለከተ ለአቻዎቻቸውና ለተለያዩ የማኅበረሰቡ ክፍሎች ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ በስፋት መሥራት እንደሚገባቸውና በሥራውም ወቅት ቦርዱ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግላቸው ለሠልጣኝ ተማሪዎቹ ተገልጾላቸዋል። ተማሪዎች በበኩላቸው በሥልጠናው ወቅት በተነሱ ርዕሰ-ጉዳዮች ላይ በቂ ግንዛቤ እንዳገኙ ገልጸው፤ በቀጣይም የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን ለመሥራት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።




