Skip to main content

የኢትዯጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሁለተኛ ዙር የምርጫ ጣቢያዎችን በዲጂታል ሲስተም የመመዝገብ ሥራ ማከናወን ጀመረ

የኢትዯጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንደ አዲስ ከተቋቋመበት 2011 ዓ.ም. አንሥቶ አንድ ሀገራዊ ምርጫ እና ሦስት ሕዝብ ውሣኔዎችን ማስፈጸሙ ይታወቃል። ቦርዱ በቀጣይም የ7ኛውን ዙር ሀገራዊ ምርጫ ለማከናወን የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል።

ስለሆነም ቦርዱ በቀጣይ የሚያከናውናቸው ምርጫዎች ከዚህ በፊት ከተካሄዱት ምርጫዎች በአፈጻጸም ቀልጣፋና ጊዜው የሚጠይቀውን ዘመናዊነት የተከተሉ ለማድረግ፤ የምርጫ ጣቢያ እና የምርጫ ክልል ጽ/ቤቶች በተለያዩ ባለድርሻ አካላት በርቀታቸው፣ በመልካ-ምድራዊ አቀማጣቸው የታወቁ እና የተለዩ እንዲሁም ለመራጩ ሕዝብ ምቹና ተደራሽ እንዲሆኑ፣ በተጨማሪም ሕግን መሠረት አድርገው የተቋቋሙ መሆናቸዉን የማረጋገጥ እና መረጃዎች በተሟላ መንገድ የማደራጀት ሥራ አስፈላጊ በመሆኑ፤ ምርጫ ጣቢያዎቹ የሚገኙበት ትክክለኛ ቦታዎች የGIS ቴክኖሎጂን በመጠቀም በ‘’XY Coordinate’’ የመለየት እና የመመዝገብ ሥራ እያከናወነ ይገኛል።

በዚሁ መሠረት በመጀመሪያ ዙር በሲዳማ፣ በድሬደዋ፣ እና በሐረሪ ክልሎች እንዲሁም ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጌዲዮ ዞን ላይ በ3495 ምርጫ ጣቢያዎች ላይ ’የ XY Coordinate’’ ምዝገባ የተከናወነ ሲሆን፤ በሁለተኛ ዙር ደግሞ በደቡብ ኢትዮጵያ፣ በማዕካላዊ ኢትዮጵያ እና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች በተጨማሪም ከአሮሚያ ክልል በጅማ ዞን ላይ በ9643 የምርጫ ጣቢያዎች ከግንቦት 3 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ የምርጫ ጣቢያዎች ምዝገባ እያከናወነ ይገኛል።

ይህ የምርጫ ጣቢያዎች ምዝገባ በቀጣይ በሶማሌ፣ በአፋር፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ እና በጋምቤላ ክልሎች ላይ ከግንቦት 25 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ የሚቀጥል ሲሆን፤ በቀሪ የሀገሪቱ ክልሎች ላይ ደግሞ ከሐምሌ 2017 ዓ.ም. ጀምሮ የምርጫ ጣቢያዎችን ’በXY Coordinate’’ ላይ የመመዝገብ ሥራው የሚከናወን ይሆናል።

Share this post