Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አጋርነት መድረክ አስፈላጊነት ላይ ውይይት ተካሄደ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ግንቦት 5 ቀን 2017 ዓ.ም. ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች (ሲ.ማ.ድ) ጋር የሚኖር የአጋርነት መድረክ አስፈላጊነት ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሄደ። ውይይቱን በንግግር የከፈቱት የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ወ/ሮ ሜላትወርቅ ኃይሉ ሲሆኑ፤ በንግግራቸውም ምርጫ ቦርድ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምርጫን በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ለሚኖራቸው ተሣትፎ ዕውቅና ከመስጠት አንሥቶ አብሮ እስከመሥራት የደረሰ ግንኙነት እንዳለው አስታውሰው፤ ይኽም ሲሆን ሚናን በመለየት ተባብሮ መሥራቱ የምርጫን ነፃና ገለልተኛ እንዲሁም ዲሞክራሲያዊነቱን በማረጋገጥ ረገድ ከፍ ያለ አስተዋፅዖ ያለው በመሆኑ እንደሆነ ተናግረዋል። በዚኽም መድረክ ላይ ማኅበራቱ በምርጫ ትምህርትም ላይ ባላቸውም ተሣትፎ ይሁን እንደታዛቢ በሚኖራቸው ኃላፊነት መሻሻል የሚገባቸውን እየለዩ መሄድና የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

ስለአጋርነት መድረኩ ዋና ዋና ዐላማዎች፣ ከፕሮግራሙ ስለሚጠበቀው ውጤት፣ ስለአሠራሩ መነሻ ሃሳብ፣ እንዲሁም የሲ.ማ.ድ የተሣትፎ ሁኔታ እና የአሠራሩን አጠቃላይ ሂደት በተመለከተ አጠቃላይ ማብራሪያ በቦርዱ ባለሞያ የተሰጠ ሲሆን፤በማስከተልም ቦርዱ በመራጮች ትምህርት ላይ ከተሠማሩ ሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች ጋር ያለው አጋርነት አስፈላጊነትና ቀደም ሲል የነበረው የአጋርነት ልምድን የተመለከተ ገለጻ በቦርዱ የሲቪክና የመራጮች ትምህርት ሥራ ክፍል ኃላፊ አቶ ነብዩ ተክሌ አማካኝነት የተሰጠ ሲሆን፤ በምርጫ መታዘብ ላይ ከተሠማሩት ጋር ያለውን የተሣትፎ ልምድን በተመለከተ ደግሞ በውጭ ግንኙነትና አጋርነት ማጎልበቻ የሥራ ክፍል ኃላፊ አቶ ድንቁ ወርቁ አማካኝነት ገለጻ ተሰጥቷል። ከማኅበራቱ ጋር የሚደረጉ የትብብር መድረኮችን በተመለከተ ያሉትን ተሞክሮዎች ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ልምድ አንጻር የኮሚሽኑ የአጋርነት ሥራ ክፍል ኃላፊ በሆኑት የምሥራች ለገሠ አማካኝነት ማብራሪያ የተሰጠ ሲሆን፤ የኮሚሽኑን አመሠራረትና የአሠራር የሕግ ማዕቀፎችንም በተመለከተ ኃላፊዋ ጨምረው አብራርተዋል። ተሣታፊዎችም ተሞክሯቸውን ያካፈሉ ሲሆን፤ በቡድን በቡድን በመሆንም የምርጫ አጋርነት መድረክ አስፈላጊነት፣ የአባልነት መሥፈርቱ፣ ዐላማዎቹ፣ በየምን ያኽል ጊዜ መድረኩ መገናኘት ያስፈልገዋል የሚለውና የመገናኛ ቦታዎች፣ የመድረኩ አወቃቀር እንዴት መሆን አለበት፣ ውጤታማ የማስተዳደር ዘይቤዎች እንዲሁም ከመሳሳይ መድረኮች ጋር ሊኖር ስለሚገቡ ግንኙነቶችን በተመለከተ እንዲወያዩና የደረሱበትንም ስምምነት እንዲያጋሩ ተደርጓል።

በመጨረሻም የቦርድ አመራር አባል የሆኑት ብዙወርቅ ከተተ ተሣታፊዎቹ ስለሰጡት ገንቢ አስተያየት አመስግነው ከየቡድኑ የፆታ ተዋጽኦን በጠበቀ መልኩ አንድ አንድ ሰው ተወክሎ ወደሚቀጥለው ሥራ ጊዜ ሳይሰጡ መቀጠል እንደሚያስፈልግ ባሳሰቡት መሠረት ከቦርዱ ጋር አብረው የሚሠሩ አምስት ጊዜያዊ የቴክኒክ ቡድኖች ተመርጠዋል፡፡ ሌላኛው የቦርድ አመራር አባል የሆኑት ዶ/ር አበራ ደገፋ በበኩላቸው ሥራው የቦርዱን የሕግ ማዕቀፎች በተከተለ መልኩ እንዲሆን አሳስበዋል።

Share this post