Skip to main content

ቦርዱ የፓለቲካ ፓርቲዎችን አቅም ለመገንባት የፓለቲከኞችን የምርጫ ክህሎት ለማጎልበት ሥልጠና መስጠት ጀመረ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከኔዘርላንድ የመድብለ ፓርቲ የዲሞክራሲ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ከተለያዩ የፓለቲካ ፓርቲዎች ለተውጣጡ ፓለቲከኞች በምርጫ ክርክር ክህሎት ላይ ስልጠና እየሰጠ ይገኛል።

የሥልጠናው ዋንኛ ዓላማ ፓለቲከኞች ለመራጩ የሚያቀርቡት ማኒፌስቶ (ፓሊሲዎችና ፕሮግራሞች) የህዝብ ቅቡልነት እንዲያገኙ የፓለቲከኞች የምርጫ ክርክር ክህሎትን ማሳደግ ላይ ያተኮረ ነው።

በምርጫ ክርክር አማካኝነት ተፎካካሪ የፓለቲካ ፓርቲዎች ለመራጩ ህዝብ በሚሰጡት አማራጭ የፓሊሲ አማራጮች ምክንያት መራጮች ዕውቀት ላይ ተመስርተው የሚበጃቸውን እንዲመርጡ ከማስቻሉ ባሻገር የዲሞክራሲ ተሳትፎ ባህልን ይጎለብታል።

በሥልጠና የመክፈቻ መርሃ ግብር ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሮ ሜላትወርቅ ኃይሉ 7ኛውን ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ ለማካሄድ አንድ ዓመት ገደማ ነው የቀረን። ስለሆነም ይህ ስልጠና የክርክር ክህሎታችሁን በማጎልበት የተደራጀ የፓለቲካ ፕሮግራሞቻችሁን፣ ፓሊሲዎቻችሁን ለመራጩ በማስተዋወቅ እና በማሳመን፤ መራጩ መረጃና ዕውቀት ላይ ተመስርቶ እንዲመርጥ ያስችለዋል ብለዋል።

ሥልጠናው ከሚሸፍናቸው ርዕሰ ጉዳዮች መካከል የፓለቲካ ክርክር ምንነት እና መርሆች፣ የተግባቦት ጉልበት ለምርጫ ክርክር ያለው ፉይዳ፣ የክርክር ሞዴሎች አይነት እና አተገባበር፣ ለውጤታማ ክርክር ሊተገበሩ የሚገባቸው ስትራቴጂዎች እና ስልቶች እንዲሁም ውጤታማ የፓለቲካ ፕሮግራም እንዴት ይቀረፃል የሚሉ ይገኙበታል።

ሥልጠናው ከጥላቻ ንግግር፣ እርስ በርስ ከመዘላለፍ፣ ብሎም ግጭት ከሚጭሩ ንግግሮች ለመታቀብ ገንቢና አካታች በሆኑ አጀንዳዎች ላይ ፓለቲከኞች እንዲያተኩሩ ያበረታታል።

ይህን መሠል ስልጠና ፓለቲከኞች በሚከውኑት አርአያነት እና ገንቢነት ባለው ተግባቦት፤ ውጥረት የነገሰበትን የፓለቲካ ከባቢ እንዲረግብ ያግዛል። ሥልጠናው ውድድሩ ከፍተኛ ትንቅንቅ በበዛበት የፓለቲካ ምህዳር ውስጥ ፓለቲከኞች የተግባቦት ክህሎታቸውን ስለሚያሳድጉ ፓሊሲዎቻቸውን በሚያቀርቡት ውጤታማ የምርጫ ክርክር አማካኝነት መራጮች በምርጫ ተግተው እንዲሳተፉ ያስችላል፡፡

በአራት ዙር የተዘጋጀው ስልጠና ንድፈ ሃሳብ እና የተግባር የምርጫ ልምምድን (Mock election debates) አቀናጅቶ እንደሚሰጥ ታውቋል። የመጀመሪያው ዙር ስልጠና ከሚያዚያ 29 አስከ ግንቦት 1 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚሰጥ ታውቋል፡፡

Share this post