ዓሲምባ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲን በተመለከተ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተሰጠ ውሳኔ
እነ ዶሪ አስገዶም ዓሲምባ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ/ዓዴፓ/ በሚል ስያሜ በ26/2/2012 ዓ.ም የክልላዊ የፖለቲካ ፓርቲ ህጋዊ የእውቅና ጥያቄ ለቦርዱ አቅርበው በምዝገባ ሂደት ላይ የነበሩ ሲሆን፤ የፓርቲው ህጋዊ የእውቅና ፈቃድ ሂደት በአገራችን በተከሰተው ጦርነት ምክንያት ተቋርጦ ቆይቶ በኋላም እነ ሐጎስ ወልዱ በቁጥር ዓዴ-0027/15 በቀን 25/07/2015 ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ ተቋርጦ የነበረው ሂደት እንዲቀጥል በማለት አመልክተዋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በድጋሚ በቁጥር ዓዴ-0032/15 በቀን 16/09/2015 ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ ጊዜያዊ የእውቅና ፈቃድ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡
ቦርዱም በሀምሌ 5 ቀን 2015 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ ዓሲምባ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ የተባለ ክልላዊ ፓርቲ ለመመስረት በ26/2/2012 ዓ.ም ለቦርዱ ጥያቄ አቅርበው የነበረው እነ አቶ ዶሪ አስገዶም መሆናቸውን እና በወቅቱ ከቀረበው የመስራች አባላት ዝርዝር ውስጥ እነ አቶ ሐጎስ ወልዱ ባለመኖራቸው እና የዓሲምባ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አደራጅ ኮሚቴ ባልሆኑበት ሁኔታ የፓርቲ ምዝገባ ሂደቱን ለማስቀጠል የሚጠይቁበት አግባብ የለም በማለት ውሳኔ ሰጥቷል፡፡
ቦርዱ በሰጠው ውሳኔ ላይ እነ አቶ ሐጎስ ወልዱ በቀን 5/12/2015 ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ የዓሲምባ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ መስራች አባላት አይደላችሁም በማለት ጥያቄው ተቀባይነት የለውም መባሉ አግባብ አለመሆኑን ጠቅሰው የውሳኔ ማስተካከያ እንዲደረግላቸው የጠየቁ ሲሆን ቦርዱ በድጋሚ በቁጥር አ1162/11/1372 መስከረም 08/2016 ዓ.ም የቀድሞውን ውሳኔ ሊያስቀይር የሚችል ምክንያት አልተገኘም በማለት ውሳኔውን አጽንቶታል፡፡
በመቀጠልም እነ ዶሪ አስገዶም በቁጥር Adp0079/16 በቀን 11/01/2016 ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ በአሁኑ ሰአት የተሻለ ሰላም በመኖሩ የተቋረጠው ሂደት እንዲቀጥል እና ህጋዊ የሰውነት ማረጋገጫ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡
ቦርዱም ፓርቲው የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት ጳጉሜ 4 ቀን 2012 ዓ.ም በትግራይ ክልል ባካሄደው ህገ ወጥ ምርጫ የተሳተፈ በመሆኑ ህዳር 10 ቀን 2016 ዓ.ም ከቦርዱ በተጻፈ ደብዳቤ ማንኛውም አባላቸው የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በህግ የተጣለበትን በሀገሪቱ ውስጥ የሚንቀሳቀሱም ሆነ በፖለቲካ ፓርቲነት ለመመዝገብ የሚደራጅን አካል የመመዝገብ፣ የመቆጣጠር እና የመደገፍ ስልጣን በተመለከተ ግልጽ አቋሙን እንዲያሳውቅ በጠየቀው መሰረት በቁጥር 0073/16 በቀን 12/03/2016 ዓ.ም በተጻፈ መልስ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በህግ የተጣለበትን በሀገሪቱ ውስጥ የሚንቀሳቀሱም ሆነ በፖለቲካ ፓርቲነት ለመመዝገብ የሚደራጅን አካል ለመመዝገብ፣ ለመቆጣጠር እና ለመደገፍ የተሰጠውን ስልጣን ተቀብለው እንደሚንቀሳቀሱ ገልጸዋል፡፡
ቦርዱም ህዳር 19 ቀን 2016 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ የፓርቲው የምዝገባ ሂደት እንዲቀጥል፣ አደራጅ ኮሚቴው ጥቅምት 25 ቀን 2012 ዓ.ም ያደረገው መስራች ጉባኤ ላይ የቦርዱ ተወካዮች እንዲገኙ ባለማሳወቁ በጉባኤው የተካሄዱ የአመራር ምርጫም ሆነ በጉባኤው የተወሰኑ ውሳኔዎች ያልተመዘገቡ መሆኑን፣ አደራጅ ኮሚቴው ጉባኤ ከመካሄዱ 30 ቀናት አስቀድሞ ቦርዱ ታዛቢ እንዲመድብለት እንዲያሳውቅ እና ረቂቅ የፓርቲውን ደንብ፣ ፕሮግራም እና እና መመስረቻ ጽሁፍ ለቦርዱ በማቅረብ መስራች ጉባኤውን በድጋሚ እንዲያካሂድ ወስኗል፡፡
ፓርቲው በቁጥር Adp0075/16 በቀን 14/05/2016 ዓ.ም የፓርቲው አባላት የሚገኙበት ኢሮብ ወረዳ ከግማሽ መሬት በላይ በኤርትራ ሰራዊት ቁጥጥር ስለሚገኝ በአካባቢው ተንቀሳቅሶ አባላት ማደራጀት ስለማይችል የኤርትራ ሰራዊት የተጠቀሱትን አካባቢዎች እስከሚለቅ እና የተዘጋው መንገድ እስከሚከፈት ድረስ ለጉባኤው በቂ ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ፓርቲው ከቦርዱ ምንም አይነት ጊዜያዊም ሆነ ቋሚ ህጋዊ እውቅና እና የምዝገባ ፈቃድ ሳያገኝ በቦርዱ ህጋዊ እውቅ እና ፍቃድ እንደተሰጠው በማስመሰል በተለያዩ መድረኮች አሳሳች መግለጫ እንደሚሰጥ ቦርዱ ተረድቷል፡፡
ቦርዱም በቀን 23/07/2017 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ ፓርቲው የጀመረውን ህጋዊ እውቅና የማግኘት ሂደት ቦርዱ እንዲያሟላ የጠየቃቸውን መስፈርቶች በራሱ ጊዜ ሳያሟላ አንጠልጥሎ ሳይጨርስ የቀረ በመሆኑ፣ እንዲሁም ፓርቲው የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ማህበረሰቡን የሚያሳስቱና የሚያደናግሩ በመሆኑ፤ ፓርቲው ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ምንም አይነት ጊዜያዊም ሆነ ቋሚ ህጋዊ እውቅና እና የምዝገባ ፈቃድ ያልወሰደ እና እና የምዝገባ ሂደቱን ያልጨረሰ በመሆኑ ህብረተሰቡ ይህን ተረድቶ ጥንቃቄ እንዲያደርግ በአክብሮት እናሳውቃለን፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ
ሚያዚያ 14 ቀን 2017 ዓ.ም
