Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የበጎ ፈቃደኝነት አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ለሆኑ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ስልጠና ሰጠ።

የቦርዱ የስነ-ዜጋና መራጮች ትምህርት የስራ ክፍል የስነ-ዜጋና መራጮች ትምህርትን ለሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል ተደራሽ ለማድረግ ከተለያዩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እና ሌሎች አጋር አካላት ጋር በጋራ እየሰራ ይገኛል።

ትምህርቱን በመላው ሀገሪቱ በስፋት ተደራሽ ለማድረግ የበጎ ፈቃደኝነት አገልግሎት የሚሰጡ ወጣቶችን ከየክልሉ በመመልመል በየአካባቢያቸው ለማሰማራት እቅድ የያዘ ሲሆን በቦርዱ የሲዳማ ክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በኩል ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ለተውጣጡ 25 የሁለተኛ እና ሦስተኛ ዓመት ተማሪዎች ከሚያዝያ 4 እስከ 5 /2017 ዓ.ም የቆየ የሁለት ቀናት የመጀመሪያ ዙር ስልጠና ሰጥቷል።

ስልጠናው ከቦርዱ ዋና መስሪያ ቤት እና የሲዳማ ክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በተውጣጡ ባለሙያዎች የተሰጠ ሲሆን ሰልጣኝ ተማሪዎቹ በስነ-ዜጋና መራጮች ትምህርት ይዘት፥ ትምህርቱን በስፋት የማዳረሻ ዘዴዎች እና ትምህርቱ የሚያስፈልጋቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች ልየታ ላይ በቂ ግንዛቤ እንዳገኙ ተስተውሏል።

ሰልጣኝ ተማሪዎቹ ከስልጠናው ያገኙትን እውቀትና ክህሎት ተጠቅመው በየአካባቢያቸው ለሚገኙ ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ስለምርጫ እና ተያያዥ ጉዳዮች ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ እንደሚሰሩ በስልጠናው ማጠናቀቂያ ወቅት ገልፀዋል። የቦርዱ ባለሙያዎች በበኩላቸው ሰልጣኝ ተማሪዎቹ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራውን በሚጀምሩበት ወቅት አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርጉላቸው በማስገንዘብ ስራውን በዘላቂነት ለማስቀጠል ግንኙነታቸው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

Share this post