የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች በምርጫ ሂደት ትርጉም ባለው አግባብ እንዲሳተፉ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የድርሻቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በአካታችነት ማዕቀፍ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች በ7ኛው ሀገር አቀፍ ጠቅላላ ምርጫ በመራጭነት እና በተመራጭነት የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር እየሰራ ይገኛል።
ይህን ዕቅድ ዕውን ለማድረግ ቦርዱ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን የምርጫ ፍላጎት ለመለየት እና ተሳትፎ ለማሳደግ ኢስት አፍሪካ የተባለ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ቀጥሮ ሀገራዊ ጥናት በማስጠናት ላይ ይገኛል።
አጥኚ ድርጅቱ አጥንቶ ባቀረበው ረቂቅ የጥናቱ ግኝቶች ላይ ለመወያየት በተዘጋጀ የአንድ ቀን አውደ ጥናት ላይ መልዕክታቸውን ያስተላለፉት የቦርዱ ሰብሳቢ ወ/ሮ ሜላትወርቅ ኃይሉ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን በምርጫ ሂደት የማሳተፍ ትርጉም ያለው ስራ የቦርዱ ጏላፊነት ብቻ ሳይሆን፤ መንግስትን ጨምሮ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሠራር እና ትብብርን ይጠይቃል ብለዋል።
የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች በ7ኛው ሀገር አቀፍ ጠቅላላ ምርጫ እንዲሳተፉ የባለድርሻ አካላት የጏላፊነት ድርሻ በጥናቱ በግልፅ ሊመላከት ይገባል ያሉት ወ/ሮ ሜላትወርቅ የጥናቶቹ ግኝቶች ተጨባጭ እና ትክክለኛ መረጃ ላይ ተመስርተን ተግባራዊ ውሳኔ እንድንሰጥ ሊያግዙን ይገባል ብለዋል።
በቀረበው የጥናቱ ግኝቶች እና ምክረ ሀሳቦች ላይ የቦርዱ ሥራ አመራር አባላት፣ የሥራ ክፍል ኃላፊዎች፣ ባለሙያዎች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት የጥናት ሰነዱን ለማዳበር የሚያግዙ ገንቢ ሀሳብ ግብዓቶች ሰጥተዋል።
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሥራ አመራር አባል የሆኑት ወ/ሮ ብዙወርቅ ከተተ በበኩላቸው አጥኚ ድርጅቱ የተሰጡ ግብዓቶችን በሚገባ አካቶ በተቻለ ፍጥነት የተጠቃለለ ሪፖርት እንዲያቀርብ አፅንኦት ሰጥተው ተናግረው ይህን ጥናት በማስተባበር ውጤታማ እንዲሆን በመትጋት ላይ የሚገኙትን የቦርዱን ሥርዓተ ጾታና ማህበራዊ አካታችነት የሥራ ክፍል ባለሙያዎችን፣ በአውደ ጥናቱ ግብዓት ለሰጡ የቦርዱ ሥራ አመራሮች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።


