Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የህጻናት ፓርላማ ምስረታ ሥልጠና እና ሙያዊ ድጋፍ ሰጠ!

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ መንግስት አንቀጽ 102 መሰረት ምርጫን የማስፈጸም ሥልጣን የተጣለበት ገለልተኛ ተቋም ነው፡፡ በመሆኑም ዜጎች በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ እና በምርጫ ሂደት ዙሪያ ግንዛቤን ያገኙ ዘንድ ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡ በዚህም መሰረት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የህጻናት ፓርላማ ባካሄደው የምስረታ እና የሥራ አስፈጻሚዎች ምርጫ ላይ በቦርዱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በኩል የምርጫ ኦፕሬሽን እና የሥነ ዜጋ እና መራጮች ትምህርት ሥራ ክፍሎች ባለሙያዎች በምርጫ ሂደት እና በዴሞክራያዊ መብት ልምምድ ዙሪያ ሥልጠና ሰጥተዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በምርጫዉ አጠቃላይ ሂደት ላይ ሙያዊ እና የምርጫ ቁሳቁሶችን ማለትም፣ ድምጽ መስጫ ሳጥን፣ የሚስጥር ድምጽ መስጫ መከለያ (ቡዝ) እና ሌሎች የምርጫ ማስፈጸሚያ ቁሳቁሶችን በውሰት ድጋፍ በማድረግ የምርጫ ሂደቱ የዴሞክራሲዊ የምርጫ መርሆዎችን የተከተለ እንዲሆን አስተዋጽዖ አድርጓል፡፡ ህጻናት የወደፊት መራጭም ተመራጭም እንደመሆናቸዉ መጠን የዴሞክራያዊ ምርጫ ሒደትን ከወዲሁ ልምምድ ያደርጉ ዘንድ ድጋፍ ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይህን መሰል ተግባር ለወደፊትም አጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡

Share this post