የ7ኛው ጠቅላላ ሀገር አቀፍ ምርጫ የዕቅድ ዝግጅት ምክክር ተጀመረ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የ2018 በጀት ዓመት ዓመታዊ ዕቅድ እና የ7ኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ ዕቅድ ዝግጅት ላይ የቦርዱ ሥራ አመራር አባላት፣ የቦርዱ ሥራ ክፍል ኃላፊዎችና የክልል ቅርንጫፍ ፅ/ቤት የሥራ ክፍል ኃላፊዎች በታደሙበት አውደ ጥናት አካሄደ።
የ7ኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ ዕቅድን ከወዲሁ ማዘጋጀት ያስፈለገበት ዓላማ ምርጫውን ሕጉ በሚፈቅደው የምርጫ የጊዜ ሠሌዳ ለማካሄድ ዕቅዱን ለኢ.ፌ.ዲ.ሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመላክ ለምርጫ ማስፈፀሚያ ሥራው የታለመው በጀት በወቅቱ እንዲፀድቅ ለማስቻል ያለመ ነው።
የቦርዱ ሰብሳቢ ወ/ሮ ሜላትወርቅ ኃይሉ እንዳሉት በ2018 ዓ.ም ለምናካሂደው የ7ኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ ዝርዝር፣ የሚለካ፣ ወጪ ቆጣቢ እና በጊዜ የተገደበ ብሎም ለእያንዳንዱ የምርጫ ተግባሮቻችን ምክንያታዊ እና ተጨባጭ በጀት ለማዘጋጀት ይህን አውደ ጥናት አዘጋጅተናል ብለዋል።
የ2018 በጀት ዓመት ዓመታዊ ዕቅድ እና የ7ኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ ዕቅድ ለማዘጋጀት የቦርዱን የአምስት ዓመት ስትራቴጂያዊ ዕቅድ መሠረት በማድረግ የቦርዱ የየሥራ ክፍሉ ኃላፊዎች የየሥራ ክፍሎቻቸውን ዕቅድ በማቅረብ በቀረቡ መነሻ ዕቅዶች ላይ በርካታ ዕቅዶቹን የሚያጎለብቱ የማሻሻያ ሃሳቦች ከአውደ ጥናቱ ታዳሚው ለመሰብሰብ ተችሏል።
የዕቅድ ዝግጅቱ ቦርዱ የምርጫ ሂደቶችን በራሱ ሙሉ አቅም የሚያከናውንበትን ተቋማዊ አቅም ታሳቢ አድርጓል። በረቂቅ የዕቅድ ዝግጅቱ ቦርዱ 7ኛውን ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ለማድረግ እየሠራ መሆኑም ተመላክቷል።
ወ/ሮ ሜላትወርቅ ምርጫውን ነፃና ገለልተኛ ለማድረግና የምርጫ ሥራዎቻችንን ለማቀላጠፍ መንግስትን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላት የተለመደ ድጋፋቸውን ካደረጉልን ቢያንስ የመራጮች እና የእጩዎችን ምዝገባ በቴክኖሎጂ ታግዘን ለማከናወን ከፍተኛ ጥረት እናደርጋለን ብለዋል።
በጠቅላላ ምርጫው በአካታችነት ማዕቀፍ አካል ጉዳተኞች፣ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች፣ የሕግ ታራሚዎች እና መሠል የማህኅበረሰብ ክፍሎች በምርጫ ሂደቱ የነቃ ተሳትፎ እንዲኖራቸው በቦርዱ ያላሰለሰ ጥረት እንደሚደረግ ተገልጿል።
የዕቅዱ ዝግጅት የሁሉም የቦርድ አመራር አባላት፣ የቦርዱ የሥራ ክፍሎች ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች የጋራ እርብርብ እና ውጤት መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
