Skip to main content

ቦርዱ አካል ጉዳተኞች በቀጣይ ምርጫዎች ትርጉም ያለው ተሳትፎ እንዲኖራቸው የዳሰሳ ጥናት እያስጠና መሆኑ ተገለፀ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አካል ጉዳተኞች በ6ኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ የነበራቸውን ተሳትፎና ውክልና ምን ይመስል እንደነበረ አማካሪ ድርጅት ቀጥሮ በማስጠናት ላይ ይገኛል።

የዳሰሳ ጥናቱ ዋነኛ ዓላማ እነዚህ የማህበረሰብ ክፍሎች የፓለቲካ ተሳትፎቸው ውስን እንዲሆን ያደረጓቸውን ችግሮች ነቅሶ በማውጣት በቀጣይ በሚኖሩ ምርጫዎች ትርጉም ያለው ተሳትፎ እንዲኖራቸው ቦርዱ እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ሊተገብሯቸው የሚገቡ ምክረ ሃሳቦችን ለማመላከት ያለመ ነው።

በዋልያ ማኔጅመንት አማካሪ ድርጅት የተጠናውን የዳሰሰ ጥናት ለመገምገም እና የዳሰሳ ጥናቱን በሃሳብ ግብዓቶች ለማዳበር በተዘጋጀ አውደ ጥናት (validation workshop) ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሮ ሜላትወርቅ ኃይሉ የአካል ጉዳተኞች በፖለቲካና በሕዝብ አስተዳደር የነቃ ተሳትፎ እና ትርጉም ያለው ውክልና እንዲኖራቸው ለማስቻል ሁላችንም ባለድርሻ አካላት በከፍተኛ ኃላፊነት ልንረባረብ ይገባል ብለዋል።

የትክክለኛና ጤናማ የዴሞክራሲ ሥርዓት መገለጫ አንዱ የሁሉም ድምፅ የሚሰማበት የምርጫ ሥርዓት መገንባት ነው ያሉት ወ/ሮ ሜላትወርቅ በቦርዱ አማካኝነት በአማካሪ ድርጅት የተደረገው ጥናት ባለፈው ምርጫ የነበረው አካል ጉዳተኞችን የማካተትና የመወከል ሂደት ምን እንደሚመስል በመገምገም ሊስተካከሉና ሊፈፀሙ የሚገባቸውን ጉዳዩች ከመለየት አንስቶ የእርምት እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል ተግባራዊ ጥናት ይሆናል ብዬ እጠብቃለሁ ብለዋል።

የዳሰሳ ጥናቱ የሸፈናቸው ቦታዎች የአዲስ አበባ ከተማ፣ ኦሮሚያ፣ ሲዳማ፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ኢትዮጵያ እና ሐረሪ ክልሎች ናቸው።

በዳሰሳ ጥናቱ የአካል ጉዳተኞች በምርጫ ሂደት የነበራቸው ተሳትፎ እና ውክልና በዋኘኛነት ከፖሊሲና ከሕግ ማዕቀፎች፣ ከተቋማዊ አደረጃጀት፣ ከመራጮች ምዝገባና ትምህርት፣ ከምርጫ ጣቢያዎች ተደራሽነት እና ምቹነት፣ ከአመለካከት እና መሰል ጉዳዮች አንፃር እንደተገመገመ ማወቅ ተችሏል።

በአውደ ጥናቱ የማጠቃለያ መርሃ ግብር ላይ ንግግር ያደረጉት የቦርዱ ሥራ አመራር አባል ወ/ሮ ብዙወርቅ ከተተ በአውደ ጥናቱ ተሳታፊዎች የተሰነዘሩ ጥናቱን የሚያሻሽሉ አግባብነት ያላቸው የሃሳብ ግብዓቶች በአጥኚው አማካሪ ትኩረት ተሰጥቷቸው እንዲካተቱ አፆንኦት ሰጥተው የተናገሩ ሲሆን፤ አውደ ጥናቱ የታለመለትን ዓላማ እንዲመታ የአውደ ጥናቱን ተሳታፊዎች፣ የአጥኚውን ድርጅት እና የቦርዱን የሥርዓተ ጾታና ማህበራዊ አካታችነት ሥራ ክፍል ባለሙያዎች አመሠግነዋል።

በዳሰሰ ጥናቱ በ6ኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ የመረጡና በምርጫ ሂደቱ ያልተሳተፉ አካል ጉዳተኞች፣የፓለቲካ ፓርቲዎች፣ የግል ተወዳዳሪዎች፣ የሀገር ውስጥ እና የውጪ ምርጫ ታዛቢዎች፣ በአካል ጉዳተኞች ላይ የሚሠሩ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ የቦርዱ ሥራ አመራር አባላት፣ የቦርዱ የሥራ ክፍል ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች ተሳታፊ መደረጋቸው ተገልጿል።

Share this post